የቻይና ልማት ባንክ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት አጠናክሮ ለመቀጠል ዝግጁ መሆኑን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከኢትዮጵያ ጋር በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን የትብብር ዘርፎች ያለውን ግንኙነት አጠናክሮ ለመቀጠል ዝግጁና ቁርጠኛ መሆኑን የቻይና ልማት ባንክ የአሜሪካና አፍሪካ ዓለም አቀፍ ትብብር ዲፓርትመንት ጄነራል ሀላፊ ቢያን ሺዩን ገለጹ
በቤጂንግ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ከቻይና የልማት ባንክ የአሜሪካና አፍሪካ ዓለም አቀፍ ትብብር ዲፓርትመንት ጄኔራል ሀላፊ ቢያን ሺዩን ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱም በኢትዮጵያና በቻይና ልማት ባንክ መከካል ያለው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝና በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተከሰተው ግጭት በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደረ እና ኢኮኖሚው ይህን ጫና ተቋቁሞ በማደግ ላይ የሚገኝና ተስፋ ሰጪ ነው ተብሏል፡፡
ባንኩ በሂደት ላይ ላሉ የልማት ፕሮጀክቶችና ለኢትዮጵያ የፋይናንስ ፖሊሲ ተቋማት የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲሁም በ8ኛው የቻይና አፍሪካ ትብብር ፎረም የሚኒስትሮች ኮንፈረንስ የልማት ትብብር ግቦች መሰረት ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል አምባሳደር ተሾመ ጥሪ አቅርበዋል።
ባንኩ ከፈረንጆቹ ከ2007 ጀምሮ የኢትዮጵያ ቁልፍ የልማት አጋር ሆኖ የቀጠለ መሆኑን እና የፋይናንስና የልማት ተቋማት ጋርም መልካም ትብብር ያለው መሆኑን የገለጹት ደግሞ ቢያን ሺዩን ናቸው፡፡
ባንኩ ከኢትዮጵያ ጋር በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን የትብብር ዘርፎች ያለውን ግንኙነት አጠናክሮ ለመቀጠል ዝግጁና ቁርጠኛ መሆኑን መግለጻቸውን በቤጂንግ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።