Fana: At a Speed of Life!

ከኤርትራ ጋር የጋራ ጥቅሞቻችንን መሰረት በማድረግ በትብብር እየሰራን ነው – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከኤርትራ ጋር የጋራ ጥቅሞቻችንን መሰረት በማድረግ በትብብር እየሰራን እንገኛለን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸምን ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት አቶ ደመቀ እንደገለጹት ፥ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር መልካም የሚባል ግንኙነት አላት።

ከኤርትራ ጋር የጋራ ጥቅምን መሰረት በማድረግ በትብብር እየተሰራ እንደሆነ ገልጸው ፥ ግንኙነቱን ወደ ጠንካራ የኢኮኖሚ ትብብር ለማሸጋገር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

“የድንበር አካባቢ ንግድና የሰዎች ዝውውሮችን የሚያሳልጡ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች፣ የወደብ አጠቃቀም፣ የንግድ ልውውጥ፣ የጉምሩክ፣ የኢሚግሬሽንና የመሳሰሉ የሁለቱን አገሮች ህዝቦች ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ የትብብር ማዕቀፎችን ለማበጀት ትኩረት ሰጥተን እየሰራን እንገኛለን” ብለዋል።

በውጭ አገሮች የሚኖሩ የሁለቱ አገሮች ዳያስፖራዎች የተባበረ ድምጽ አወንታዊ ሚና እንደተጫወተም ገልጸዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የኢትዮ-ኬንያ ግንኙነት አስመልክቶ በተለይም ከአጎራባች አገሮች ጋር ያለውን የልማት ትስስርና ግብይት በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያና ኬንያ መካከል ያለው ታሪካዊ ግንኙነት አሁንም በመልካም ሁኔታ መቀጠሉን ተናግረዋል።

የሁለቱ ሀገሮች የድንበር አካባቢ ፀጥታ፣ የመሰረተ ልማት ትስስር እንዲሁም የንግድና የኢኮኖሚ ግንኙነትን ለማጠናከር የሚያስችሉ ስምምነቶች ተደርገው በሂደት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የሁለቱን ሀገሮች ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከርና የህዝቦችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተመረጡ የትኩረት መስኮች ላይ መተባበር የሚያስችል ልዩ ስምምነት መደረጉንም አስታውሰዋል።

ለኢትዮጵያ ወጪና ገቢ ምርቶች በአማራጭነት ያገለግላል ተብሎ የሚታሰበው የኬንያው ላሙ ወደብ ፕሮጀክትም ሁለቱን ሀገሮች ተጠቃሚ የሚያደርግ ትልቅ የመሰረተ ልማት አካል መሆኑንም አቶ ደመቀ ገልጸዋል።

የገቢና ወጪ ንግድ ልውውጡን በአንድ የጋራ ቁጥጥር ማዕከል ለማስተናገድ የሚያስችል አሰራር በጋራ ተዘርግቶ ስራ መጀመሩንም አስታውሰዋል።

በድንበር አካባቢ የሚኖሩ የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ተጠቃሚ ለማደረግ የድንበር ንግድ ረቂቅ ስምምነት ተዘጋጅቶ ለውሳኔ መቅረቡንም ጠቁመዋል።

ሁለቱን ሀገራት በኤሌክትሪክ ኃይል ለማስተሳሰር የተጀመረው ጥረትም በጥሩ አፈፃፀም ላይ መሆኑን ጠቅሰው ፥ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታው በሐምሌ ወር መጨረሻ ሃይል ማስተላለፍ ይጀምራል ብለዋል።

የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ በሐምሌ 2014 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ሃይል ማስተላለፍ እንዲጀምር ሁለቱ አገሮች ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም ሁለቱን ሀገሮች ሊያስተሳስሩና ለቀጣናዊ ትብብርና ለህዝቦች ተጠቃሚነት ከፍተኛ ሚና ያላቸው የተጀመሩ የጋራ ፕሮጀክቶች ፍጻሜ እንዲያገኙ የቅርብ ክትትል ይደረጋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.