ባለፉት አስር ወራት ከቆዳና ቆዳ ውጤቶች ዘርፍ 33 ነጥብ 14 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ተገኘ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት አስር ወራት ከቆዳና ቆዳ ውጤቶች ዘርፍ 33 ነጥብ 14 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱ ተገለፀ፡፡
በቆዳና ቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል የዕቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ብርሃኑ እንደተናገሩት፥ ባለፉት አስር ወራት 69 ነጥብ 21 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 33 ነጥብ 14 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ማግኘት ተችሏል፡፡
በጫማና በቆዳ ውጤቶች 104 ነጥብ 6 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ ምርት ለሀገር ውስጥ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ 144 ነጥብ 6 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በማቅረብ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ጫና መቀነስ መቻሉንም ገልፀዋል፡፡
ባለፉት አስር ወራት 8 ሺህ 120 ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል በቆዳና ቆዳ ውጤቶች ዘርፍ መፈጠሩን እና በአጫጭር ስልጠናዎች 579 ሰዎች በቆዳ ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ሀይል ማፍራት መቻሉንም ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል በንዑስ ዘርፉ አራት ምርምሮችንና 87 የምርት ማልማት ስራዎችን ወደ ኢንዱስትሪው ለማስተላለፍ ታቅዶ ሁለት የምርምር ውጤቶች እና በቆዳና ቆዳ ውጤቶች እና በጫማ ውጤቶች የለሙ 93 ዲዛይኖች ወደ ኢንዱስትሪ ማስተላለፍ ተችሏል ነው የተባለው፡፡
ከአካባቢ ጥበቃ በተያያዘ በበጀት አመቱ 22 የቆዳ ፋብሪካዎች ሁለተኛ ደረጃ ፍሳሽ ማጣሪያ እንዲጠቀሙ ታቅዶ 21 ማብቃት መቻሉን ከቆዳና ቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡