Fana: At a Speed of Life!

በአፋር ክልል የኩፍኝ መከላከያ ክትባት ከነገ ጀምሮ ይሰጣል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፋር ክልል የኩፍኝ መከላከያ ክትባት ከነገ ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት እንደሚሰጥ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ ጤና ቢሮ እድሜያቸው ከ6 ወር እስከ 23 ወር የሚሆናቸው ከ200 ሺህ በላይ ሕጻናት ክትባቱን እንደሚወስዱ ገልጿል።

የአፋር ክልል የጤና ቢሮ የእናቶችና ሕጻናት ክትባት ዳይሬክተር አቶ አወል ጉደሌ ፥ አሸባሪው ህወሓት በክልሉ በፈጸመው ወረራ ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸዉ ሰዎች በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች መሰባሰባቸውንና የሕጻናት ክትባት ስራዉ በመስተጓጎሉ ለበሽታው አጋላጭ ሁኔታዎች መኖራቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።

በሽታውን ቀድሞ መከላከልን ታሳቢ በማድረግ ከግንቦት 10 እስከ 14 ቀን 2014 ዓ.ም በክልሉ በሁሉም ወረዳዎች እድሜያቸው ከ6 ወር እስከ 23 ወር የሚሆናቸው ከ200 ሺህ በላይ ሕጻናት የኩፍኝ ክትባት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

ክትባቱ በጤና ተቋማትና በተመረጡ ቦታዎች እንደሚሰጥና የክልሉ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶችና የማህበረሰብ መሪዎች ለክትባት ዘመቻው ውጤታማነት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ኩፍኝ ሚዝል በተባለ ቫይረስ አማካኝነት የሚከሰት ተላላፊ በሽታ ሲሆን ፥ በሽታዉ በወቅቱ ካልታከመ የአይን ብርሃን ማጣት ፣ ለሳንባ ምች፣ ለአንጎል እብጠትና ተያያዥ ኢንፌክሽን ያጋልጣል።

በሽታው በየትኛዉም እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን የሚያጠቃ ቢሆንም በተለይም ሕጻናት በተለየ ሁኔታ እንደሚያጠቃ ይነገራል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.