Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ከተሞች ጉባዔ በኬንያ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ከተሞች ጉባዔ በምዕራብ ኬንያ ባሕር ዳርቻ በምትገኘው ኪሱሞ ከተማ ዛሬ ተጀምሯል፡፡

ጉባዔው በመካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ የአፍሪካ ከተሞች በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚያጋጥሟቸውን በርካታ ፈተናዎች ለማቃለል እና ቀጣይነት ያለው ዕድገት እንዲያስመዘግቡ ለመደገፍ ያለመ ነው ተብሏል፡፡

ከተሞች ሥደተኞችን እና ተፈናቃዮችን በመቀበል ረገድ በሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች ፣ መፍትሄዎች እና ችግሮቹን በማቃለል ረገድ መወጣት ስለሚገባቸው ሚናም ምክክር እንደሚካሄድ በወጣው መርሃ-ግብር ላይ ተመላክቷል፡፡

ጉባዔው በከተሞች አስተዳደር እና ኢንቨስትመንት ላይ የሚመክር ሲሆን ፣ ከአፍሪካ የተውጣጡ ሚኒስትሮች እና የአፍሪካ ከተሞች ከንቲባዎች ተገናኝተው በጉባዔው በተነሱ ዝርዝር ነጥቦች ላይ እና የቀጣይ ሦስት ዓመታት ፍኖተ ካርታ ላይ ተወያይተው ስምምነት ላይ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአፍሪካ በመካከለኛ ደረጃ የሚገኙ ከተሞች አጀንዳ 2030ን ዕውን ለማድረግ ባላቸው ራዕይ ላይ እና በተሻለ ዕቅድ እና አገልግሎት አህጉሪቱን ከድህነት አረንቋ በማላቀቅ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በአፍሪካ ኅብረት በተወጠነው አጀንዳ 2063 ላይም ምክክር ይካሄዳል፡፡

በጉባዔው ከ70 የተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ከ8 ሺህ በላይ ልዑካን እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

ጉባዔው ዛሬን ጨምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት እንደሚካሄድ ዘ ኢስት አፍሪካና ሲቲ አሊያንስ ዘግበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.