የጦርነትን ውድመት ለማስቀረት ሁሉም ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጥ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጠየቁ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጦርነትን ውድመት ለማስቀረት ሁሉም ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጥ ኢዴህ እና ነእፓ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጠየቁ፡፡
አሸባሪው የህወሓት ቡድን ህፃናትን ጨምሮ በትግራይ ክልል የሚገኙ ዜጎችን በግዳጅ ወደ ጦር ሜዳ እያዘመተ መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች ዓለም አቀፍ ተቋማት እያወጡ ሲሆን ፓርቲዎቹ ሁኔታውን ኮንነዋል፡፡
ህፃናትና አዛውንትን ጨምሮ በርካታ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች በህወሓት የሽብር ቡድን እየተገደዱ ወደ ጦርነት እየተማገዱ መሆናቸው ይታወሳል።
ወደ ጦር ሜዳ የማይሄዱት ላይ ደግሞ እስርን ጨምሮ የገንዘብ መቀጮ እንደሚጣልባቸው መረጃዎች ያመላክታሉ።
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት (ኢዴህ) ሊቀመንበሩ አቶ ገብሩ በርሃ ፥ የሽብር ቡድኑ ከዚህ ቀደም የትግራይን ህዝብ ባላመነበት ጦርነት መማገዱን አስታውሰው ከትናንት ድርጊት ባለመማር ዳግም ወደ ግጭት ለመግባት የሚደረጉ አካሄዶችን አሳዛኝ ሲሉ ይገልጿቸዋል፡፡
የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ምክትል ሊቀመንበር ዘኑር አብዱልዋህብ ፥ ለዳግም ጦርነት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተቀባይነት የላቸውም ነው ያሉት፡፡
በግጭቱ ውስጥ ተፋላሚ የሆኑ ወገኖች ንግግርን እንዲያስቀድሙም ጠይቀዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ህፃናትን ወደ ጦር ግንባር መላክ ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀል መሆኑን አንስተው ፥ ሆኖም የሽብር ቡድኑ በተደጋጋሚ መሰል ድርጊቶችን ሲፈጽም መቆየቱን አክለዋል።
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢዴህና የነእፓ ፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች ፥ ወደ ሌላ ዙር ጦርነት ላለመግባት የሚደረጉ ትንኮሳዎች እንዲቆሙና ለሰላም መስራት እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡
በአፈወርቅ እያዩ