የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትና የጥላቻ ንግግርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ መንግስት በአግባቡ እንዲያስፈጽም የሕግ ባለሙያዎች ጠየቁ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትና የጥላቻ ንግግርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ መንግስት በአግባቡ ሊያስፈጽም ይገባል ሲሉ የሕግ ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የሕግ ባለሙያዎቹ አቶ ፋሲል ስለሺ እና ሙስጠፋ ሺፋ÷ አዋጁ እየተተገበረ ባለመሆኑ ዜጎች ላይ አሉታዊ ጫናዎች እየደረሱ ነው ብለዋል፡፡
አዋጁን በግልጽ እየጣሱ የሚገኙ ግለሰቦች ቢበራከቱም፥ ሕግ ማስከር ላይ መንግስት ዳተኝነት እየታየበት መሆኑንም አብራርተዋል።
በማህበራዊ ሚዲያና በመደበኛ የመገናኛ ብዙሃን ሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግርን የሚያሰራጩ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ አዋጁ ቢደነግግም፥ መንግስት ለጉዳዩ በቂ ትኩረት እንዳልሰጠም ነው ባለሙያዎቹ ያነሱት፡፡
የሕግ አማካሪና የጥብቅና ባለሙያዎቹ÷ መንግስት አጥፊዎች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ እስከታችኛው መዋቅር የዘለቀ ሕጋዊ አሰራር ዘርግቶ እንዲሠራ ጠይቀዋል፡፡
በሀቅ ማጣራት ላይ ጥናትና ምርምር የሚያደርጉት እና የመርሳ ሚዲያ ኢንስቲቲዩት ባልደረባ ሄኖክ ሰማ እግዜር በበኩላቸው፥ የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትና የጥላቻ ንግግሮች ከሚያሳድሩት ዘርፈ ብዙ ቀውስ አንጻር መገናኛ ብዙሃን ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡
ሚዲያ ተቋማት ሀቅን የሚያጣራ ዴስክ ማቋቋም እንደሚገባቸው ጠቁመው፥ የጥላቻ ንግግሮችና ሀሰተኛ መረጃዎች በግዴለሽነት እንዳይተላለፉ መገናኛ ብዙሃን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል፡፡
በአወል አበራ