Fana: At a Speed of Life!

ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የገቡ ተማሪዎች ሙሉ ትኩረታቸውን በትምህርታቸው ላይ ሊያደርጉ ይገባል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ያለፉትን ዓመታት ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፈው ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የገቡ ተማሪዎች ሙሉ ትኩረታቸውን በትምህርታቸው ላይ ሊያደርጉ እንደሚገባ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች ገለጹ።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በባህር ዳር ከተማና በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ያነጋገራቸው አዲስ ገቢና ነባር ተማሪዎች እንዲሁም የከተማዋ ነዋሪዎች ፥ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የተሰባሰቡ ወጣቶች ለአንድ ዓላማ ፣ ለትምህርት የሚከትሙባቸው ተቋማት ናቸው ብለዋል።

ስለዚህም ተማሪዎች ሙሉ ትኩረታቸው የመጡበትን የትምህርት ዓላማ ማሳካት ሊሆን ይገባል ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፥ ተማሪዎች የፖለቲካ መጠቀሚያ ሊያደርጓቸው ከሚሹ አካላትም ራሳቸውን መጠበቅ እንደሚገባቸው ነግረውናል።

በጉዳዩ ላይ ሃሳባቸውን የሰጡን የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ወላጅ አባት አቶ ጥበቡ ይሁኔ፥ ‘‘ተማሪዎች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚፈጠሩ ነገሮች ተዋናይ እንጂ ደራሲ አይደሉም’’ ሲሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአስተዳደር አካላትም ተማሪዎቻቸዉ መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ሃላፊነታቸዉን መወጣት ፣ ወላጆችም ልጆቻቸው ትምህርታቸው ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ መምከርና መገሰፅ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ሌላው አስተያየት ሰጪ አበረ መዓዛም ፥ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ያሉባቸው አካባቢዎች ማህበረሰብ ተማሪዎችን የፖለቲካ መጠቀሚያ ሊያደርጓቸው ከሚፈልጉ አካላት መጠበቅና በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ማገዝ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ያሉ የተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሰሞኑ ለአንደኛ ዓመት ተማሪዎቻቸው የምዝገባ ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል።

በፀጋዬ ወንድወሰን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.