Fana: At a Speed of Life!

በቸኮሌት መጠቅለያ የኮኬን ዕፅ ይዞ ከኢትዮጵያ ለመውጣት የሞከረ ግለሰብ በ12 ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጣ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቸኮሌት መጠቅለያ የኮኬን ዕፅ ይዞ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከኢትዮጵያ ለመውጣት የሞከረው የውጭ አገር ዜጋ በ12 ዓመት ፅኑ እስራትና በ75 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጣ ፍርድ ቤት ወሰነ።

አርፋን ሀይደር የተባለው የውጭ አገር ዜጋ መስከረም 11 ቀን 2014 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ሲሆን በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ከአዲስ አበባ ወደ ኳታር ሃገር ዶሃ ለመጓዝ ሲል በተደረገበት ፍተሻ በእጁ በያዘው ቦርሳ ውስጥ በቸኮሌት መጠቅለያ የተጠቀለለ 5 ሺህ 200 ግራም የሚመዝን የኮኬን ዕፅ ይዞ መገኘቱ ተመላክቷል፡፡

ተከሳሹ በፈፀመው የናርኮቲክ ሳይኮትሮፒክ መድሐኒቶች ወይም ዕፆችን ይዞ መገኘት ወንጀል በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳች ዐቃቤ ህግ ዳይሬክቶሬት ጄነራል ክስ ተመስርቶበታል።

ተከሳሽ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ቀርቦ ክሱ ደርሶትና ተነቦለት የእምነት ክህደት ቃሉን ሲጠየቅ ” እኔ ድርጊቱን አልፈፀምኩም ጥፋተኛም አይደለሁም ”ሲል ቃሉን በመስጠት ክዶ ተከራክሯል ።

ዓቃቤ ህግ በበኩሉ የተከሳሽን ጥፋተኝነት ለፍርድ ቤቱ ያስረዱልኛል ያላቸውን ዝርዝር የሰው߹የሰነድና ኢግዚቢትነት አቅርቦ በበቂ ሁኔታ ለችሎቱ በማስረዳቱ ግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተላልፏል ።

በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ ተከሳሽ ከዚህ በፊት የጥፋተኝነት ሪከርድ የሌለበት በመሆኑ አንድ የቅጣት ማቅለያ በመያዝ ተከሳሽ በ12 ዓመት ፅኑ እስራትና በ75 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጣ መወሰኑን ከፍትሕ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.