Fana: At a Speed of Life!

በእርቅ ወደ ተሻለ ነገር መራመድ ጊዜው የሚጠይቀው ተግባር ነው – ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የእርቅን ጥቅም በመቀበል ወደ ተሻለ ነገር መራመድ ጊዜው የሚጠይቀው ተግባር መሆኑን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትረያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ገለጹ፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የ2014ን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ በከፈቱበት ወቅት ÷ ህዝቡን ወደ እርቅና ወደ ይቅርታ ማምጣት የሃይማኖት አባቶች ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

ሠላም ለሃይማኖት መጠበቅና ለህዝብ ደኅንነት መረጋገጥ ትልቅ ዋጋ እንዳለውም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አውስተዋል።

ሰው ሁሉ ሠላምን ቢጠብቅ በሁሉ ነገር ስኬታማ መሆን እንደሚቻል የገለጹት ፓትረያርኩ÷ በአገሪቱ በተከሰቱ እና ግጭቶች ህዝቡ መንገላታቱን ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ የሚታየው ነገር ራስን የማስበለጥ እና የሌላውን የማሳነስ መሆኑን ጠቁመው ÷ይህን ተግባር በማረም በመተሳሰብ ፣ በትህትናና በፍቅር መመለስ እንደሚገባም አስረድተዋል።

በተጨማሪም ቅዱስ ጉባዔው ራሱን ከማናቸውም አደረጃጀቶች ነጻ በማድረግ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ሠላም መሥራትና መጣር ይጠበቅበታል ነው ያሉት ቅዱስነታቸው፡፡

ሠላምንና አንድነትን ለማረጋገጥ ጉልበትን እንደ አማራጭ መውሰድ በማቆም የተከሰቱትን ችግሮች በውይይትና በድርድር ለመፍታት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ጥረት እንዲያደርጉም ፓትርያርኩ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በቅድስት ብርሃኑ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.