ሀገራዊ ሀብትን በማሰባሰብ የኢንቨስትመንት አሰራሮች እንዲጎለብቱ የሚደግፈው ዓለም አቀፍ ተቋም ኢትዮጵያን በአባልነት ተቀበለ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራት የውስጥ ሀብታቸውን በማሰባሰብ በሙያዊ ዲሲፕሊን እንዲጠቀሙ እና የኢንቨስትመንት አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ድጋፍ የሚያደርገው “ዓለም አቀፉ የሶቨረን ሀብት ፈንድ ፎረም” ኢትዮጵያን በአባልነት ተቀበለ።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ ፎረሙ በአባልነት ተቋሙን መቀበሉን አመልክቷል።
ፎረሙ በተለይ አባላት ሀገራዊ ሀብትን በማሰባሰብ መልካም አስተዳደርን እና የኢንቨስትመንት አሰራሮችን እንዲያጎለብቱ ድጋፍ ያደርጋል።
የመንግስት እና የፋይናንስ ተቋማት በተጠቀሱት አሰራሮች ዙሪያ ጥልቅ መረዳት ኖሯቸው መርሆዎችን እንዲተገብሩ ይሰራል ነው የተባለው።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በአባልነት መታቀፉን ተከትሎም የፎረሙን መርሆዎች በፈቃደኝነት እንደሚተገብርም አስታውቋል።
ዓለም አቀፉ የሶቨረን ሀብት ፈንድ ፎረም ከ40 በላይ ሀገራትን በአባልነት አቅፏል።