Fana: At a Speed of Life!

የደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ከጎብኚዎች 330 ሚሊየን ብር ገቢ አገኘ

አዲስ አበባ፣ግንቦት 10፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ክልሉን ከጎበኙ የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች 330 ሚሊየን ብር ገቢ መገኘቱን ገለጸ፡፡

የቢሮው ምክትል ሃላፊና የቱሪዝም ዘርፍ ሃላፊ ወይዘሮ ፍሬህይወት ዱባለ ÷ የሰላም እጦትና ሌሎችም ችግሮች የቱሪዝሙን ዘርፍ እየፈተኑት ቢመጡም ቢሮው የሀገር ውስጥ ቱሪዝም እንዲስፋፋ በልዩ ትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት 2ሚሊየን 931 ሺህ የአገር ውስጥ እና 27 ሺህ 883 የውጭ ጎብኝዎች መጎብኘታቸውን ያስታወቁት ወይዘሮ ፍሬህይወት÷ የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎች ቁጥር እንዲጨምር ተከታታይ ስራ እየተሰራ እንደሆነም አመላክተዋል፡፡

የቱሪዝሙ ዘርፍ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ58 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠሩን ጠቅሰው÷ አሁንም ተጨማሪ የስራ እድሎች በየደረጃው እንዲፈጠሩ ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ ማስረዳታቸውን ከክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የሚጎበኙ ቦታዎችን ለቱሪስቶች ምቹ እንዲሆኑ በቂ የመሰረተ ልማት ከማሟላት ባሻገር አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጥራት ያለውና ደረጃውን የጠበቀ መስተንግዶ እንዲያደርጉ ቢሮው ተከታታይነትና ወጥነት ያለው ስራ እየሰራ እንደሆነም አንስተዋል፡፡

የደቡብ ክልል ባህልና ተፈጥሮ ላይ የተመሰረተ የዳበረ የቱሪዝም ሀብት ያለው ክልል መሆኑን አንስተው÷ አሁን ካሉት የጎብኝዎች መዳረሻ በተጨማሪ በቀጣይ የአርባ ምንጭ አዞ እርባታ ማዕከል፣የታማ ጥብቅ የዱር እንስሳት ማዕከልና የአምበርቾ ኢኮ ቱሪዝም ቦታዎችን የጎብኝዎች መዳረሻ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.