Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው ሸኔ በሚንቀሳቀስባቸው የተለያዩ አካባቢዎች በተወሰደ እርምጃ ህዝቡ አንፃራዊ ሰላም እያገኘ ነው-ኮ/ል አበበ ገረሱ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሸባሪው ሸኔ ቡድን በሚንቀሳቀስባቸው ዞኖች በተወሰደ እርምጃ ህዝቡ ከነበረበት ስጋት እና ጭንቀት በመላቀቅ አንፃራዊ ሰላም እያገኘ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ጸጥታ እና አስተዳደር ቢሮ ገለጸ።
የቢሮ ምክትል ሃላፊ ኮሎኔል አበበ ገረሱ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ አሁን ላይ የጸጥታ ሃይሉ ከማህበረሰቡ ጋር እየወሰደ ባለው የተቀናጀ እርምጃ ሸኔ እንደበፊቱ ስጋት አይሆንም ብለዋል።
በክልሉ ጉጂ ዞኖች፣ በአራቱ ወለጋ ዞኖች፣ በሰሜን እና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች እንዲሁም በከፊል ምስራቅ ሸዋ ዞን የሸኔ ቡድንን ከአካባቢው የማጽዳት እርምጃ መወሰዱን ጠቁመዋል፡፡
ህዝቡ ከመንግስት እና ከፀጥታ ሃይሉ ጋር የቆመ እና የሸኔ ቡድን እያደረሰበት ከነበረው ግፍ እና በደል ለመላቀቅ በእርምጃው ወቅት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉንም አንስተዋል፡፡
ማህበረሰቡ በሸኔ ላይ እየተወሰደ ባለው እርምጃ መረጃ በመስጠት እና ምግብን ከፀጥታ ሃይሉ ጋር ተቋድሶ በመብላት አብሮ ውሎ በማደር እርምጃው ውጤታማ እንዲሆን አድርጓል ነው ያለት።
በአከባቢዎቹ ተገድቦ የቆየው የህዝብ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅሳቃሴ ወደ መደበኛው ቦታ እየተመለሰ መሆኑን ኮሎኔል አበበ ገረሱ ተናግረዋል።
አሁን ላይ ሸኔ የፀጥታ ስጋት የማይሆንበት ደረጃ ላይ ይገኛል ያሉት ኮሎኔል አበበ ገረሱ÷ ሆኖም ግን በተወሰኑ አካባቢዎች የቆየውን የጸጥታ ችግር ምክንያት በማድረግ ዝርፊያ ለመፈጸም የሚሞክሩ ግለሰቦች መኖራቸውን አንስተዋል።
ስለሆነም ህዝቡ ከጸጥታ ሃይሉ ጋር ተቀናጅቶ የሸኔ ቡድን እንዳስወገደ ሁሉ የአካባቢውን ጸጥታ ለማደፍረስ ከሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች አካባቢውን በመጠበቅ ሊያስወግድ ይገባል ብለዋል።
በመሰል ድርጊት የሚሳተፉ ግለሰቦች እንቅስቃሴያቸውን በማጥናት ህዝቡ ለፀጥታ ሃይሉ መረጃ እንዲሰጥም ምክትል ሃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።
በሸኔ ሽብር ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ቡድኑ እስኪጸዳ ድረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ኮሎኔል አበበ አስገንዝበዋል፡፡
በበላይ ተስፋዬ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.