Fana: At a Speed of Life!

የስቶክ ገበያን ለማቋቋም የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የስቶክ ገበያን በኢትዮጵያ ለማስጀመር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ፣ በገንዘብ ሚኒስቴር እና ኤፍ ኤስ ዲ አፍሪካ መካከል ተፈረመ።
 
ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ማሞ ምህረቱ እንዲሁም የኤፍ ኤስ ዲ ዋና ስራ አስፈጻሚ ማርክ ናፒየ ተፈራርመውታል።
 
ስምምነቱ የስቶክ ገበያን ወይም የሰነደ መዋዕለ ነዋይ ገበያን ለማቋቋም የሚያስፈልገውን የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ የሚያቀርብ መሆኑ ተገልጿል፡፡
 
የስቶክ ገበያው ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ለሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የገቢ ማሰባሰቢያ መድረኮችን እንደሚፈጥርም ይጠበቃል።
 
ባለፉት ዓመታት መንግስት ኢኮኖሚውን ለማሳደግ በርካታ ለውጦችንና ማሻሻያዎችን ያደረገ ሲሆን÷ የሰነደ መዋዕለ ንዋዮች ገበያ መጀመር ደግሞ ከግሉ ዘርፍ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ ይረዳል ተብሏል።
 
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ በአገራችን ታሪክ የመጀመሪያ የሆነው እና በመንግስት እና በግሉ ዘርፍ ጥምረት የሚቋቋመው የስቶክ ገበያ ለኢትዮጵያ ፋይናንስ ኢንዱስትሪ እና ለአጠቃላይ ኢኮኖሚው አዲስ ዘመንን የሚያበስር ነው ብለዋል።
 
በትብብር ስምምነቱ መሰረት ኤፍ ኤስ ዲ አፍሪካ የሰነደ መዋዕለ ንዋዮች ገበያውን ለማስጀመር የሚያስፈልጉ ወጪዎችን የሚሸፍን ይሆናል።

 

ለተጨማሪ መረጃ ሊንኩን ይጫኑ  https://www.youtube.com/watch?v=Q6O0bhiYG3Q

በታሪኩ ለገሰ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.