Fana: At a Speed of Life!

በርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን የተመራ ልዑክ ወርቅ የሚያመርቱ ማኅበራትን ጎበኘ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን የተመራ ልዑክ ተደራጅተው ወርቅ በማምረት ላይ የሚገኙ ማኅበራትን ጎበኘ፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰንን ጨምሮ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሀያት ካሚል፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ እና የፌደራል እንዲሁም የክልል አመራሮች በኩርሙክ ወረዳ የተደራጁ ሦስት የወርቅ ማኅበራትን የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል፡፡
ወርቅ አምራች ማኅበራቱ ከትንሽ ካፒታል ተነስተው ከራሳቸው አልፎ ለበርካቶች የስራ እድል መፍጠራቸውን ገልጸው÷ ስራቸውን ወደተሻለ ደረጃ ለማሳደግ መንግስት ከቀረጥ ነጻ የሚገቡ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችና ስራውን በእውቀት ለመምራት የሚያስችል የስልጠና ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሀያት ካሚል÷ የጉብኝቱ አላማ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን ከኢንተርፕራይዞች ጋር ለማስተሳሰር፣ የክህሎት ክፍተቶችንና የቴክኖሎጅ ፍላጎቶችን ለይቶ መሙላት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ማኅበራቱ ወደ ኢንተርፕራይዝ ለማደግና እርስ በእርስ ትስስር ፈጥረው በቴክኖሎጅ የተደገፈ ስራ በመስራት ለሌሎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ለዚህም ሚኒስትር መስሪያ ቤታቸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የስልጠናና ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎችን ያደርጋል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.