Fana: At a Speed of Life!

ኩዌት ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የትብብር መስኮች ለማስፋት ፅኑ ፍላጎት እንዳላት ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኩዌት ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የትብብር መስኮች ለማስፋት ፅኑ ፍላጎት እንዳላት የኩዌት የማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ገለፀ፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ከኩዌት የማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ረዳት አብዱል ዐዚዝ ዐብዱሰላም ሹዐይብ ጋር ተወያይተዋል።
አቶ ንጉሱ በውይይቱ ላይ÷ ስለሁለቱ ሀገሮች ታሪካዊ መልካም ግንኙነት እና መንግስታቸው ይህን ግንኙነት ለማጠናከር ያለውን ፅኑ ፍላጎት ገልፀዋል።
የሀገራችንን አሁናዊ ሁኔታና የሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ተልዕኮና ሚና በማብራራት በተለይም በሰለጠነ የሰው ሀይል አቅርቦት ረገድ ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ ሀብትና በዚህ ረገድ የሁለቱ ሀገራት ትብብርና በጋራ መስራት ለሕዝቦቻቸው ያለውን ፋይዳ አስረድተዋል።
ዐብዱልዐዚዝ በበኩላቸው÷ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የትብብር መስኮች ለማስፋት ፅኑ ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል፡፡
በሰው ሀይል ስምሪት ብቻ ሳይሆን የበጎ አድራጎት ሥራዎች፣ ግብርናና ተያያዥ መስኮች ላይ በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው÷ በዚህ ረገድ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት እንደምትሻ አረጋግጠዋል፡፡
ለዚህም የትብብር መነሻ ይሆን ዘንድ የመግባቢያ ሰነድ ለመፈራረም ዝግጁ እንደሆኑ አስረድተው÷ የልዑካን ቡድኑን ጉብኝት ታሳቢ በማድረግ በነርሱ በኩል ያዘጋጁትን ረቂቅ ሰነድ ለሚኒስትር ዴኤታው ማስረከባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.