በኮምቦልቻ ከተማ ከ800 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የመንገድ ፕሮጄክት ሥራ በይፋ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኮምቦልቻ ከተማ ከ800 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የመንገድ ፕሮጄክት ሥራ በይፋ መጀመሩን ከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡
የኮምቦልቻ ከተማ ከንቲባ አቶ መሀመድ አሚን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ የከተማዋን የመንገድ ችግር እንደሚቀርፍ የታመነበት ፕሮጄክት በይፋ ተጀምሯል፡፡
አጠቃላይ የመንገዱ ርዝመት 7 ነጥብ 11 ኪሎ ሜትር ሲሆን ወደ ጎን 21 ሜትር ስፋት እንደሚኖረው እንዲሁም በቦርከና ወንዝ 25 ሜትር ስፋት ያለው ድልድይ እንደሚገነባም አመላክተዋል፡፡
መንገዱ አጠቃላይ ግንባታው በሁለት ዓመት እንደሚጠናቀቅ እና ለዚህም በፌዴራል መንግሥት የሚሸፈን 806 ሚሊየን ብር ወጪ እንደሚደረግበት ገልጸዋል፡፡
የመንገድ ግንባታው በተለይ ቦርከና ወንዝ ላይ ይፈጠር የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅ እንደሚፈታም ተናግረዋል፡፡
በከድር መሀመድ