ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ለአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ያሰባሰባቸውን 2 ሺህ 400 መጻሕፍት አስረከበ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ለአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ያሰባሰባቸውን 2 ሺህ 400 መጻሕፍት አስረከበ።
“ሚሊየን መጻሕፍት ለሚሊኒየሙ ትውልድ” በሚል መሪ ቃል ለአንድ ወር የሚቆይ የመጻሕፍት ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር በይፋ መጀመሩን ተከትሎ ነው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት መጻሕፍት በማሰባሰቡ ረገድ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ያለው።
ዛሬም ለቤተ መጻሕፍቱ ያስረከባቸው 2 ሺህ 400 መጻሕፍት በተለያዩ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቋንቋዎች የተፃፉ መሆናቸው ተመልክቷል።
በአብርሆት ቤተ መጻሕፍት በተከናወነው የርክክብ ስነ ስርዓት ላይ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አድማሱ ዳምጠውን ጨምሮ የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ዮናስ ዘውዴ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ዶክተር ታምራት ኃይሌ ተገኝተዋል።
የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው በስነ ስርዓቱ ላይ፥ ተቋሙ የመጻሕፍት ማሰባሰብ ሥራ አካል በመሆን የበኩሉን ኃላፊነት በመወጣቱ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማው ተናግረዋል፡፡
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከመጻሕፍት ብዛት ይልቅ ይዘት፣ ጥራት፣ በቋንቋ እና በደራሲያን ብዘሃነት ላይ ትኩረት አድርጎ ማሰባሰቡን ጠቁመው፥ በዚህም ምክንያት በሀገር ውስጥ እና በውጭ የተለያዩ ቋንቋዎች በሳይንስ፣ ታሪክ እና ሌሎች ዘርፎች የተፃፉ መጻሕፍትን ማሰባሰቡን ገልፀዋል።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ለሕዝቡ መረጃ ከመስጠት ባለፈ በተለያዩ ማኅበራዊ ኃላፊነቶች ላይ በመሳተፍ ለትውልዱ እውቀትን ለማሸጋገር እየሠራ መሆኑን ያነሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፥ የአሁኑ የመጀመሪያ ዙር መጻሕፍት የማሰባሰብ ተግባር መሆኑንና ይህም እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተወከሉት ዶክተር ታምራት ኃይሌ በበኩላቸው÷ የሚዲያ ተቋማት በመሰል ማኅበራዊ ኃለፊነቶች ውስጥ የመሳተፍ ተግባራቸውን አጠናከረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡
በየአብቃል ፋሲል