መንግስት ሕገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ በሚፈጽሙ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የንግድ ሕግና ደንብ በመተላለፍ ሕገ ወጥ ንግድ እና ኮንትሮባንድ በሚፈጽሙ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው÷ የንግድ ሕግና ደንብ በመተላለፍ የሚፈጸሙ ሕገ ወጥ ንግድ እና ኮንትሮባንድ ለሀገራችን ኢኮኖሚ እና ሕጋዊ ለሆነው የግብይት ሥርዓት ፈተና ሆኗል፡፡
ያለ ንግድ ፈቃድ መነገድ፣ ከተፈቀደ መጠንና ኮታ በላይ ምርትን ማዘዋወርና ማከማቸት፣ እጥረትን ለመፍጠር ምርት አከማችቶ መያዝ፣ ያለበቂ ምክንያት በምርቶች ላይ ዋጋ ጨምሮ መሸጥ፣ ምርቶችን አላግባብ መሰብሰብ፣ ማከማቸትና ማዟዟር፣ የንግድ ፈቃድን ለሶሰተኛ ወገን አሳልፎ መስጠት እንዲሁም የባንክ መላኪያ ፍቃድ ለሶስተኛ ወገን መሸጥ የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በማዳከም ለልማትና ለዕድገት የሚደረገውን ርብርብ እየተፈታተኑ የሚገኙ ሕገ ወጥ ድርጊቶች ናቸው ብሏል::
ይህ ሕገ ወጥነት ሀገራችን ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ በማሳጣት፣ የኑሮ ውድነትን በማባባስ እና የሀገርን ሀብት ለጎረቤት ሀገራት ሲሳይ በማድረግ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት እያስከተለ እንደሚገኝም ተመላክቷል፡፡
የጥራጥሬ ምርቶች እና የቅባት እህሎችን አላግባብ በክምችት በመያዝ ሀገሪቱ በወቅቱ ከወጪ ንግድ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ከማሳጣቱም ባሻገር÷ ምርቶች በሕገ ወጥ ንግድ እና በኮንትሮባንድ መንገድ ወደ ጐረቤት ሀገራት በመውጣት በሀገሪቱ የምግብ ሰብሎች ላይ የዋጋ ንረት እያስከተለ ይገኛል ነው ያለው መግለጫው፡፡
ሀገራችን ባላት የቁም እንሰሳት ቁጥር ብዛት በአፍሪካ ቀዳሚነትን ብትይዝም እንደ ሌሎች ምርቶች ሁሉ የቁም እንስሳት ግብይትም ለሕገ ወጥነት የተጋለጠ በመሆኑ ከዘርፉ ማግኘትየሚገባትን ገቢ እያገኘች አለመሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የጫት ምርትም ለድንበር ከተሞች ከመደበው የጫት ኮታ በላይ እንዲያልፍ በማድረግ፣ በሕጋዊ ንግድ ፈቃድ ሽፋን ከመጠን በላይ የጫት ምርት በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ውጪ በመጫን፤ ንግድ ፈቃድን በማከራየት እና መላኪያ ፈቃድን በመሸጥ የጫት ምርት የወጪ ምንዛሪ ገቢ እንዳያስገኝና ለብክነት እንዲጋለጥ መደረጉ ተገልጿል፡፡
መንግስት ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ አውጥቶ በማስገባት ዓለም አቀፍ ዋጋው ላይ ድጎማ በማድረግ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማህበረሰቡ እያቀረባቸው ካሉ ምርቶች ውስጥ ነዳጅ አንዱመሆኑ በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
ይሁን እንጂ መንግስት ምርቱን ከወጪ በማስገባት በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ እና እያሰረጨ ቢሆንም÷ በአንዳንድ የድንበር ከተሞች ከመጠን ያለፈ የነዳጅ ማደያዎች በመክፈት በውጪ ምንዛሪ የገባው የነዳጅ ምርት ለሌላ ሀገር ተሽከርካሪዎች በሕገ ወጥ መንገድ በማሰራጭት የሀገሪቱን ጥቅም እያሳጣ በሀገር ውስጥ እጥረት እንዲያጋጥም ሆን ተብሎ በመሠራት ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡
የሚስተዋለውን ሕገ ወጥነት እና ኮንትሮባንድ ለመከላከል ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ተደጋጋሚ ውይይት መደረጉን የገለጸው ሚኒስቴሩ÷ በችግሩ ውስብስብነት ምክንያት ሊፈታ ባለመቻሉ በዘላቂነት በመፍታት ሕጋዊ ንግድን ለማጠናከርና የሀገርን ተጠቃሚነትና ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማረጋገጥ የሁሉም ዜጋ፣ የንግድ ተዋንያን እና የመንግስት መዋቅር አካላትን ቁርጠኝነትና ርብርብ እንደሚጠይቅ አመልክቷል፡፡
ይህ መግለጫ ለህብረተቡ ከተገለፀበት ዕለት አንስቶ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የሕግአስፈጻሚና የፀጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ከላይ በተዘረዘሩት ሕግ ወጥ ተግባራት ላይ እጃቸው ያለበት ተሳታፊ እና ተባባሪ አካላት ላይ ተገቢውን ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንሚወስድ አስታውቋል፡፡
ስለሆነም የችግሩ ተዋንያን ከዚህ እኩይ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ በማሳሰብ ÷ በደረጃው ያለው የመንግስት አስፈጻሚ አካላትም ሚናቸውን በጽኑ በመወጣት የሀገርን ሃብትና ጥቅም የማስጠበቅ ግዴታቸውን እንዲወጡ ሚኒስቴሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡