ኢትዮጵያና ጃፓን አጋርነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር አስፈላጊውን ጥረት ለማድረግ ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰመረታ ሰዋሰው ከጃፓን ኤምባሲ እና ከጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ጋር የኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ ያተኮረ ውይይት አካሄዱ።
ሚኒስትር ዴኤታዋ በመክፈቻ ንግግራቸው እስከአሁን ለተደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን ፥ በውይይቱ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ እና የኤጀንሲው ዋና ተወካይ ሞሪሃራ ካትሱኪና ልዑካቸው ተገኝተዋል፡፡
በኢትዮጵያ በድርቅ እና በግጭት ምክንያት የተከሰተውን ሰብዓዊ ቀውስ እና የንብረት ውድመት ችግርን ለመቅረፍ ከጃፓን ተጨማሪ ዕርዳታ እንደሚያስፈልግ ጠይቀዋል።
የጃፓን ልዑካን ቡድን በበኩሉ ፥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ለማድረግ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚሆን ረቂቅ ሰነድ ያቀረበ ሲሆን ፥ በረቂቅ ሰነዱ ሶስት ጉዳዮች ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው ተገልጿል፡፡
ረቂቆቹ ሁሉን አቀፍ ልማትና ሰብዓዊ ደህንነትን ማጎልበት፣ የማይበገር ኢኮኖሚያዊ መዋቅር፣ አረንጓዴና ዘላቂ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ስርዓት መገንባት እንዲሁም በቀጣይ የሚደረግ እርዳታ እና ቴክኒካል ድጋፍ ማድረግ ላይ ያተኮሩ ናቸው ተብሏል።
ሚኒስትሯ በጃፓን ልዑካን ቡድን የተደረገላቸውን ገለጻ አድንቀው ፥ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ዘርፎች ከ10 ዓመታት ዕቅድ ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ወይዘሮ ሰመረታ ይህ መድረክ የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል።
አምባሳደር ኢቶ ታካኮ በበኩላቸው ፥ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የሚደረጉ እገዳዎች ላልተው ስልጠናዎች መጀመራቸውንና በቅርቡም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀመር ተናግረዋል።
በውይቱ በሁለቱ ሀገራት እና ህዝቦች መካከል ያለውን አጋርነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር አስፈላጊውን ጥረት ለማድረግ ስምምነት ላይ መደረሱንም ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።