Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ሌንጮ ባቲ ከሳዑዲ ዓረቢያ የንግድ ምክር ቤቶች ፌዴሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ግንቦት 12፣2014 (ኤፍ ቢሲ) አምባሳደር ሌንጮ ባቲ ከሳዑዲ የንግድ ምክር ቤቶች ፌዴሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ አጅላን አብዱልአዚዝ ጋር ንግድና ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የኢኮኖሚና የንግድ እንቅስቃሴ ለማጠናከርና ለማስፋት በሚያስችሉ ስተራቴጅዎች ላይ የመከሩ ሲሆን፥ የኢንቨስትመንት እና የንግድ ፎረም በማዘጋጀት የሳውዲ የንግድ ልዑካን ወደ ኢትዮጵያ ጉብኝት እንዲያደርጉ በሚቻልባቸው ጉዳዮችም ላይ ተወያይተዋል፡፡

የሳዑዲ ዓረቢያ የንግድ ምክር ቤቶች ምክር ቤት ፌደሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ አጅላን አብዱላዚዝ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ ኢትዮጵያ ለሳዑዲ ባለሃብቶች እንዲሁም ለሳውዲ ገበያ የምትልከውን ትልቅ የወጪ ምርት አቅም እንደሚገነዘቡ ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የኢንቨስትመንት እና የንግድ ፎረም በሪያድ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፥ የሁለትዮሽ የንግድ ትብብርን ለማስፋት ሳዑዲ ዓረቢያ ሙሉ ድጋፍ እንደምትሰጥ አረጋግጠዋል፡፡

በኢትዮጵያ እና በሳዑዲ አረቢያ መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ ለማጠናከር የኢትዮ-ሳውዲ የጋራ የንግድ ምክር ቤት መመስረት ያለውን ጠቀሜታ በተመለከተም ሁለቱ ወገኖች አፅዕኖት ሰጥተው መምከራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.