የሀገር ውስጥ ዜና

ምንጩ ያልታወቀ 9 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ንብረት አካብቷል በተባለ የቀድሞ ፖሊስ አባል ላይ ክስ ተመሰረተ

By Melaku Gedif

May 20, 2022

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከህጋዊ የወር ገቢው ጋር የማይመጣጠንና ምንጩ ያልታወቀ 9 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ንብረትና ገንዘብ አካብቶ በተገኘው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መርማሪ በነበረ ግለሰብ ላይ ክስ ተመሰረተ፡፡

በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ መርማሪ ሆኖ ሲሰራ የነበረው በላይነህ ዳጌቦ ወይም በሀሰተኛ መታወቂያ ሥሙ ተመስገን ማርቆስ እየተባለ የሚጠራው ተከሳሽ ከሚያዝያ 01 ቀን 2001 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 01ቀን 2013 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት የወንጀል መከላከልና መርማሪ ሆኖ ተቀጥሮ ሲሰራ መቆየቱ ተመላክቷል፡፡

በዚህ ወቅትም በአጠቃላይ ያገኝ የነበረው 453 ሺህ 838 ብር ሆኖ እያለ ተከሳሹ ግን በመንግስት ሥራ ተቀጥሮ ያገኝ ከነበረው ህጋዊ ገቢ ጋር በፍፁም የማይመጣጠን 8 ሚሊየን 995 ሺህ 749 ብር በሀሰተኛ መታወቂያና ማንነት በተከፈቱ የባንክ ሂሳቦች የተለያየ መጠን ያላቸውን ገንዘቦች ያንቀሳቀሰ እና ሁለት የመኖርያ ቤት ገንብቶ መገኘቱ በማስረጃዎች መረጋገጡ ነው የተገለጸው፡፡

በዚህ መሰረትም ተከሳሽ በፈፀማቸው ሀሰተኛ የህዝባዊ ድርጅት ሰነዶች መገልገል߹ በወንጀል ድርጊት የተገኘን ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ምንጩ ያልታወቀ ንብረትና ገንዘብ በማፍራት የሙስና ወንጀሎች ክስ ተመስርቶበታል፡፡

ክሱን የተመለከተው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ፀረ ሙስና ወንጀል ችሎት የተከሳሽን የመጀመርያ የክስ መቃወሚያ ለመጠባበቅ ለግንቦት 22ቀን 2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡