Fana: At a Speed of Life!

የ2ኛው ምዕራፍ የምግብ ዋስትና መርሃ ግብር በ72 ከተሞች ሊተገበር ነው

አዲስ አበባ፣የካቲት 25፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሁለተኛው ምዕራፍ የምግብ ዋስትና መርሃ ግብር በ72 ከተሞች የሚገኙ ከአንድ ሚሊየን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነው።

በመጀመሪያው ምዕራፍ መርሃ ግብር 604 ሺህ ዜጎች ተጠቃሚ መሆናቸውን የፌደራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡

የከተሞች የምግብ ዋስትና መርሃ ግብርም በዓለም ባንክ 300 ሚሊየን ዶላር፣ በኢትዮጵያ መንግስት 150 ሚሊየን ዶላር ተመድቦለት በ2009 ዓ.ም መጀመሩን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘነበ ኩሞ ገልጸዋል።

በዚህ መርሃ ግብር 92 ሺህ ዜጎች ቀጥታ ድጋፍ እያገኙ ሲሆን፥ 580 ሺህ ያህሉ ደግሞ በአካባቢ ልማት ስራ መሰማራታቸውን ጠቅሰዋል።

በአካባቢ ጥበቃ ስራ የተሰማሩት ተጠቃሚዎች በሶስት ዓመት ውስጥ ከሚያገኙት ወርሃዊ ገቢ 20 በመቶውን በመቆጠብና በሚደረግላቸው የ500 ዶላር ድጋፍ ስራ እንደሚጀምሩ ነው የተናገሩት።

በእስካሁኑ ሂደትም 58 ሺህ የሚጠጉ አባወራዎች ስልጠና ወስደው ወደ ስራ ለመሰማራት ተዘጋጅተዋል ብለዋል።

የዓለም ባንክ መርሃ ግብሩን አስመልክቶ ባካሔደው ግምገማ ውጤታማ ሆኖ በመገኘቱ ዘንድሮ በ72 ከተሞች ተጨማሪ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አቶ ዘነበ ጠቁመዋል።

በሁለተኛው ምዕራፍ የምግብ ዋስትና መርሃ ግብር ትግበራ አንድ ሚሊየን ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የዓለም ባንክ የ500 ሚሊየን ዶላር ብድርና ድጋፍ መመደቡንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ለዚሁ መርሃ ግብር 250 ሚሊየን ዶላር ይመድባልም ነው ያሉት።

ስራውን ለመጀመር የሚያስችለው አደረጃጀት እስከ መጭው ግንቦት ወር ድረስ የሚደራጅ ሲሆን፥ በቀጣይም ተጠቃሚዎች ተለይተው ወደ ስራ ይገባል መባሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.