Fana: At a Speed of Life!

“በአምባሳደርነት የተሾሙት ሁለቱ ጄነራል መኮንኖች ለተቋማዊ ለውጡ ጉልህ ድርሻ ነበራቸው” – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቅርቡ በአምባሳደርነት የተሾሙት ለአምሳደር ጀኔራል ባጫ ደበሌ እና አምባሳደር ጀኔራል ሀሰን ኢብራሂም ለሀገር መከላከያ ተቋማዊ ለውጥ ጉልህ ድርሻ እንደነበራቸው ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።

ለአምሳደር ጀኔራል ባጫ ደበሌ እና ለአምባሳደር ጀኔራል ሀሰን ኢብራሂም የምስጋናና የሽኝት ስነ ስርዓት ተካሂዷል።

በስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የመከላከያ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ሁለቱ አምባሳደር ጄነራሎች ከለውጥ በፊትና ከለውጥ በኋላ የነበራቸው አገራዊ አበርክቶ አይተኬ እንደነበር አስታውሰው እንደተቋምም እንደሃገርም በነበሩ ውጣ ውረዶችም በጋራ በመስራት ስኬታማ ቆይታ እንደነበራቸው ተናግረዋል።

መንግስት ባለው ሃላፊነት መሰረት ሁለቱን ጄነራል መኮንኖች በአምበሳደርነት መመደቡ ውጤታማ ስራ ለመስራት እንደሚያግዝ የገለፁት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፥ በቀጣይም ከአምባሳደር ጄነራሎቹ ጋር በትብብር እንደሚሰሩ እምነታቸው መሆኑን በመግለፅ መልካም የስራ ዘመን እንዲሆንላቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

አምባሳደር ጄነራል ባጫ ደበሌ ÷ተቋሙ ከዚህ በፊት መደበኛና ፕሮፌሽናል ሰራዊት ግንባታ ስራን በትክክል መስራት ባለመቻሉ በሰሜን ዕዝ ላይ የክህደት ተግባር ሊፈፀምበት እንደቻለ አስታውሰው በቀጣይም እንደተቋም በመደበኛና ፕሮፌሽናል ሰራዊት መገንባት ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

አሁን ያለንበት ወቅት ታሪካዊ ወቅት በመሆኑ አገርን ወደተሻለ ደረጃ ለማሻገር ከብሄርና ከፖለቲካ አስተሳሰብ ወገናዊነት የፀዳ ሰራዊት መገንባት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ገልፀው ይህንን ለማሳካትም በየደረጃው ያለው አመራር የራሱን ሚና ሊጫወት ይገባል ብለዋል።

አምባሳደር ጄነራል ሀሰን ኢብራሂም በበኩላቸው፥ በተቋሙ ረጅም እድሜ እንደማሳለፋችን ተቋሙ በሚፈልገው መልኩ በቅርበት ለመስራት ዝግጁ እንደሆኑ የገለፁ ሲሆን ለተደረገው የምስጋናና የሽኝት ፕሮግራም ምስጋናቸውን ማቅረባቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ፌስቡክ ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.