በክልሎች ለአመራሮች ሲሰጥ የነበረው የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ እና ጋምቤላ ክልሎች ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ሲሰጥ የነበረው የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጠናቀቀ።
ስልጠናው “አዲስ ፖለቲካዊ እይታ-አዲስ አገራዊ እመርታ ” በሚል መሪ ሀሳብ ነው ለብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ሲሰጥ የቆየው።
በሶማሌ ክልል በተካሄደው ስልጠና ማጠቃለያ ላይ በየመድረኮቹ ለተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ በበይነ መረብ ተሳትፈው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በክልሉ ምርታማነትን ለማሳደግ ለግብርናው ዘርፍ ትልቅ ትኩረት እንደተሰጠ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
በአቅም ግንባታ ስልጠናው በስትራቴጂክ ኮሙኒኬሽን፣ በፖለቲካ አመራር ፣በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ፣ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ በግብርና ልማትና ምርታማነት፣ በሰላምና ሀገራዊ አንድነት ላይ ያተኮሩ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በክልሉ ተከስቶ በነበረው ድርቅ፣ በተሰጡ ምላሾች ድርቁን መመከት እንደተቻለ ጠቅሰው÷ከፍትህ ጋር በተያያዘ ባለፉት ሦስት አመታት የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ ትኩረት እንደተሰጠ መግለፃቸውንም ከክልሉ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡፡፡
ከሙስናና ብልሹ አሠራር ጋር በተያያዘ የህዝብና የመንግሥት ሀብት ከታለመለት ዓላማ ውጭ የሚያውሉ አካላት ላይ ምርመራ እንደሚደረግና ወደ እርምጃ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
የሶማሌ ብልፅግና ፓርቲ ለክልሉ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ያዘጋጀው ስልጠና በክልሉ 5 ከተሞች ለአምስት ተከታታይ ቀናት ነው የተካሄደው።
በተመሳሳይ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ እንደገለጹት÷በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ከህብረተሰቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በተጠናከረ መልኩ ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የክልሉን ህዝብ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በመልካም አስተዳደር ተጠቃሚ ለማድረግ የአመራሩ ቁርጠኝነት ጎልቶ መታየት አለበትም ነው ያሉት።
የክልሉ የብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ላክደር ላክባክ በበኩላቸው÷ ስልጠናው ለአዳዲስ አመራሮች እና ለነባር አመራሮች መሰጠቱን ጠቅሰው÷ በቀጣይ እስከ ወረዳ እና ቀበሌ እንደሚሰጥ መግለጻቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።