Fana: At a Speed of Life!

ቢሮው አፋርን ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የሚያግዙ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው አለ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አፋርን በቀጣይ አሥር ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ተቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የሚያግዙ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

10ኛው ሀገር አቀፍ የቱሪዝም ኮንፈረንስ በሰመራ ከተማ ተካሂዷል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አህመድ አብዱልቃድር፥ አፋር የሁሉም ዓይነት የቱሪዝም መስህቦች ባለቤት ቢሆንም ለዘርፉ ተገቢው ትኩረት ሳይሰጠው መቆየቱን ገልጸዋል።

አስፈላጊው የመሰረተ ልማት ዝርጋታና የቱሪዝም ሀብቶችን የማስተዋወቅ ሥራዎች ባለመሰራታቸው እስከዛሬ የሚፈለገው ውጤት አለመገኘቱን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ክልሉን የሀገሪቱ ተቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ታቅዶ ወደ ተግባራዊ ሥራ መገባቱን ነው ያስረዱት።

ኃላፊው እንዳሉት፥ በአስር ዓመቱ መጨረሻ ክልሉን የሚጎበኙ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ቁጥር በ2011 ዓ.ም ከነበረው 12 ሺህ ወደ 80 ሺህ ለማሳደግ ታቅዷል።

“የተመረጡ ዋና ዋና የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማልማት የሚረዱ የተለያዩ ሥራዎችም ከፌዴራልና ከክልል ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለማከናወን ወደተግባር ተገብቷል” ነው ያሉት ኃላፊው።

ለእዚህም የሉሲ መካነ-ቅርስ በተገኘበት “አደአር” ላይ የሉሲ ሙዚየም ለመገንባት የዲዛይን ሥራ ተጠናቆ ግንባታውን ከቅርስ ጥበቃ ባለስልጣንና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመሆን ለመጀመር ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ክልሉ ከፌደራል መንግስት ጋር በመተባበር “ከፈንታሌ እስከ ከኤርታአሌ” የሚል ፕሮጀክት ተቀርጾ አካባቢዎቹን ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል።

ዳያስፓራውን በዘርፉ ልማት ለማሳተፍ ሰፊ ጥረት እየተደረገ መሆኑንና በቅርቡም በአካባቢዎቹ የሄሊኮፍተር ማረፊያ የሚሆን ጥርጊያ ሜዳም መዘጋጀቱን አስረድተዋል።

በተጨማሪም በአፋምቦ ወረዳ አዞና ሌሎች ብዘሃ-ህይወት የሚገኝባቸውን የገመሬ፣ ቦሃ እና አቢ ሐይቆችን ለቱሪዝም ልማት ለማዋል መታቀዱን አቶ አህመድ ገልጸዋል።

አካባቢውን ለቱሪስቶች የበለጠ ምቹና ሳቢ እንዲሆን የህብረተሰቡን ባህልና ወግ የሚያንጸባርቁ መዝናኛዎችን ለመገንባት ባለሃብቶችን የመሳብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከሰመራ ከተማ 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያለው የአለሎበድ ፍልውሃ ለጤና ቱሪዝም እምቅ አቅም ያለው በመሆኑ ወደ ፍልውሃው የሚወስድ የጥርጊያ መንገድ በዚህ ዓመት መደራቱንም ገልጸዋል።

ባለሃብቶችም በአካባቢው በአገልግሎት ዘርፉ እንዲሰማሩ ሁሉን አቀፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የቢሮ ኃላፊው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ክልሉ በዘርፉ ኢንቨስት ለማድረግ ለሚፈልጉ ባለሃብቶች መሬት በነጻ ከማቅረብ ጀምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

የቱሪዝም ኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች በአፋምቦ ወረዳ የሚገኘውን የገመሬና ቦሃ ሐይቅ ጎብኝተዋል።

የወረዳው አስተዳደር አቶ ሁሴን አሊ ወረዳው ባለው እምቅ የቱሪዝም ሃብት የወረዳው ወጣቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በባህላዊ የዕደጥበብ ውጤት፣ በአስጎብኚነትና ተያያዥ የስራ መስኮች እንደሚሰማሩ ተናግረዋል።

የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር መሀመድ ኡስማን በበኩላቸው ክልሉን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የሚደረጉ ጥረቶችን ዩኒቨርሲቲው በተለያየ መንገድ እንደሚደግፍ ገልጸዋል።

“በቱሪዝም መዳረሻ አካባቢዎች ለሚገኙ ወጣቶች በአጭርና በመካከለኛ ጊዜ ዕቅድ ስልጠናዎችን በመስጠት ተቋሙ ድጋፍ ያደርጋል።” ብለዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ ህብረተሱቡ ባህላዊ ምግቦችን በዘመናዊ መልኩ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን በሚችልበትን አግባብ ዩኒቨርሰቲው እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.