Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና ጋምቤላ አጎራባች ክልሎች ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የተጀመሩ ስራዎች ተስፋ ሰጪ ውጤት ማስመዝገባቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ አጎራባች ክልሎች ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የተጀመሩ ስራዎች ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እያስመዘገቡ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ከኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ ክልሎች የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በአካባቢዎቹ ሰላምን በዘላቂነት ማስፈን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እየመከሩ ነው።
በመድረኩ የሽብር ቡድኑ ሸኔና ሌሎች በክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች የሰላምና ፀጥታ ስጋት መሆናቸው ተነስቷል።
በዚህም በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ከመድረሱ ባሻገር ሴቶችና ህፃናት የችግሩ ሰለባ መሆናቸው ነው የተገለፀው።
መንግስት የተጠናከረ የህግ ማስከበር እርምጃዎችን እንዲወስድ የጠየቁት ተሳታፊዎቹ÷ የሰላም ግንባታና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶች እንዲጠናከሩ መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
የኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና ጋምቤላ ክልሎች ሰላምና ልማት ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍሮምሳ ሰለሞን፥ ክልሎችን በልማት ለማስተሳሰርና ሰላምን ለማስፈን እየተሰራ ነው መሆኑን ገልጸዋል።
የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማሳደግ በየደረጃው ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሰላምና ደህንነት ቢሮ ሃላፊ አቶ አቢዮት አልቦሮ በበኩላቸው ÷ የህዝቦችን አብሮነትና ወንድማማችነት ለማጠናከር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የማሳደግና በልማት የማስተሳሰር ስራዎች ውጤት በማስመዝገብ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ህብረተሰቡም እየተወሰደ ያለው ህግ የማስከበር ዘመቻ ውጤታማ እንዲሆን ህገ ወጦችን አሳልፎ መስጠት እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአፈወርቅ እያዩ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.