Fana: At a Speed of Life!

በሐረርና ጅግጅጋ አካባቢ የተተከሉት ትራንስፎርመሮች በቅርቡ ሥራ ይጀምራሉ – የኤሌክትሪክ ኃይል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረርና የጅግጅጋ ከተሞችና አካባቢያቸውን ችግር እንዲፈቱ የተተከሉት ፓወር ትራንስፎርመሮች በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምሩ የኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡
በሐረር ቁጥር 3 ማከፋፈያ ጣቢያ ሲከናወን የቆየው የፓወር ትራንስፎርመር ተከላ እና የፍተሻ ሥራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለሙከራ ዝግጁ መሆኑን በትራንስሚሽን ሰብስቴሽን ኦፕሬሽን የምስራቅ ሪጅን አስታውቋል፡፡
የሪጅኑ ዳይሬክተር አቶ ጋሻው እንድሪያስ እንዳስታወቁት÷ በማከፋፈያ ጣቢያው ባለ 50 ሜጋ ቮልት አምፔር የፓወር ትራንስፎርመር ተከላ ሥራ እና ፍተሻው በመጠናቀቁ ኃይል መስጠት የሚችልበት የሙከራ ሥራ የሚሰራበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
አዲሱ የፓወር ትራንስፎርመር መሉ በሙሉ ወደ ስራ ሲገባ በሐረር፣ በአወዳይ፣ በኮምቦልቻ ከተሞችና የገጠር መንደሮች በማከፋፈያ ጣቢያው በሚስተዋለው ከአቅም በላይ ጭነት ምክንያት ያጋጥም የነበረውን የኃይል እጥረት ሙሉ በሙሉ ይቀርፋል ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም እስከ ሐሮማያ ከተማ እንደ አስፈላጊነቱ መመገብ የሚችል አቅም የተፈጠረለት ሲሆን÷ አዲሱ ትራንስፎርመር ከነባሩ ትራንስፎርመር አቅም ጋር ሲነጻጸር በ5 እጥፍ የሚበልጥ አቅም እንዳለው ዳይሬክተሩ መናገራቸውን የኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ ያመላክታል፡፡
በተመሳሳይ በጅግጅጋ ማከፋፈያ ጣቢያ የፓወር ትራንስፎርመር ተከላ ሥራ እየተከናወነ ሲሆን÷ አፈጻጸሙም ከሐረር ቁጥር 3 ማከፋፈያ ጣቢያ ጋር ተቀራራቢ በሆነ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የሪጅኑ የሰብስቴሽን ኦፕሬሽንና ጥገና ሥራ አስኪያጅ አቶ ከድር አብደላ ገልጸዋል።
አቶ ከድር አክለውም÷ ሪጅኑ ከሑርሶ እስከ ሐረር ድረስ ባለው የ132 ኪሎ ቮልት የማስተላለፊያ መስመር ላይ አስራ ሁለት የ132ኪሎ ቮልት 400/800/1 አምፐር ከረንት ትራንስፎርመሮችን በመትከል የምስራቅ ኢትዮጵያን የግሪድ ሲስተም የሚያስተካክል ሥራ ሰርቷል ብለዋል፡፡
በሐረርና ጅግጅጋ የተተከሉትን ፓወር ትራንስፎርመሮች በቅርቡ ስራ ለማስጀመር መታቀዱ እና በሐረር ቁጥር 3 ማከፋፈያ ጣቢያ በተከናወነው የፓወር ትራንስፎርመር ተከላ ሥራ ብቻ ከ30 ሚሊየን ብር በላይ ማዳን መቻሉ ተመላክቷል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.