Fana: At a Speed of Life!

ለ2014/15 የምርት ዘመን ከ755 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ መግባቱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለ2014/15 የምርት ዘመን ወደ ሀገር ውስጥ ከሚገባው ከ1 ነጥብ 28 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን በላይ የአፈር ማዳበሪያ ከ880 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ወደብ መድረሱን የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ገለጸ፡፡
ከዚህ ውስጥም ከ755 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ የሚሆነው ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን ነው ድርጅቱ ያስታወቀው፡፡
የአፈር ማዳበሪያውን በባሕር የማጓጓዝ ስራውን ሚልክ ዌይ እና ዌስተርን በልክ የተባሉ ዓለም አቀፍ የመርከብ ድርጅቶች እያከናወኑት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ለምርት ዘመኑ የሚገባውን የአፈር ማዳበሪያ ለማጓጓዝ 23 ግዙፍ መርከቦች መመደባቸውን የኢባትሎአድ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ የሽፒንግ አገልግሎት ዘርፍ ዋና ኦፊሰር ወንድወሰን ካሳ ገልጸዋል፡፡
ከእነዚህ መርከቦች ውስጥ 13ቱ ኤን ፒ ኤስ በመባል ለሚታወቁት የአፈር ማዳበሪያ ዓይነቶች ሲሆኑ÷ 10 መርከቦች ደግሞ ለዩሪያ የተመደቡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
አጠቃላይ ከሚገባው የአፈር የማዳበሪያ መጠን 787 ሺህ ሜትሪክ ቶን ኤን ፒ ኤስ አይነቶች ሲሆን÷ ቀሪው 500ሺ ዩሪያ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በ13 መርከቦች ከሞሮኮ እተጓጓዘ የነበረው የኤን ፒ ኤስ የማዳበሪያ አይነቶች ሙሉ በሙሉ ጅቡቲ ወደብ መድረሱን የገለጹት አቶ ወንድወሰን÷ ባሳለፍነው ሳምንት ጅቡቲ የደረሰችው የመጨረሻዋ መርከብ በማራገፍ ላይ ትገኛለች ብለዋል፡
ሶስት መርከቦች ሁለቱ እያንዳንዳቸው 45 ሺህ እና አንዷ መርከብ 50 ሺህ በድምሩ 140 ሺህ ሜትሪክ ቶን ጭነው ከግንቦት 18 እስከ 21 ባሉት ቀናት ጂቡቲ ወደብ እንደሚደርሱ መናገራቸውን ከድርጅቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.