ዓለም አቀፉ የክትባት ኢኒስቲቲዩት በአፍሪካ ሶስተኛውን ማዕከል በኢትዮጵያ ከፈተ
አዲስ አበባ፣ግንቦት 15፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ የክትባት ኢኒስቲቲዩት በአፍሪካ ሶስተኛውን ማዕከል በኢትዮጵያ በአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲቲዩት በዛሬው እለት የተለያዩ እንግዶች በተገኙበት በይፋ ከፍቷል፡፡
በመርሃ ግብሩ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ ፣ በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ኮንግ ሴኦኬ ፣የዓለም አቀፉ ክትባት ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጄሮሚክም፣ በኢትዮጵያ የኮሌራ መከላከልና መቆጣጠር ፕሮጀክት ዋና ተመራማሪ ዶክተር ሲ.ኢቶን ፓርክ የተገኙ ሲሆን የኖርዌይ ጤና ሚኒስትር አማካሪ ዶክተር ቶሬ ጎዳል እና የኖርዌይ ጤና ሚኒስትር አማካሪን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች በበይነ መረብ ተሳትፈዋል፡፡
በስነ ስርዓቱ ላይ የአርማወር ሐንሰን ምርምር ኢኒስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተርን በመወከል የተገኙት ዶክተር ሻሎ ዳባ ÷ ኢኒስቲቲዩቱ ከዚህ በፊት ሲሰራበት ከነበረው ተቋማዊ ተልዕኮ በተጨማሪ ክትባትን እና መድሀኒቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት ተልዕኮ በተሰጠበት ወቅት ከዓለም አቀፉ የክትባት ኢንስቲቲዩት ጋር በአጋርነት ለመስራት ስምምነት መፍጠራችን እንደ ትልቅ እድል የሚቆጠር ነው ብለዋል፡፡
ዶክተር ደረጀ ድጉማ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያንና የደቡብ ኮሪያ ግንኙነት ረጅም ታሪክ ያለው መሆኑን አውስተው ዓለም አቀፍ የክትባት ኢንስቲቲዩት ከተቋሙ ጋር ለመሥራት ስምምነት መፍጠሩ ወቅታዊና ትክክለኛ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥም ኢትዮጵያ ትልቅ አቅም እንደምትፈጥር ተስፋ እንዳላቸው መግለፃቸውን ከኢኒስቲቲዩቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ኮንግ ሴኦኮ በበኩላቸው÷ ዓለም አቀፉ የክትባት ኢንስቲቲዩት ከአርማወር ሐንሰን የምርምር ጋር ለመስራት ዕድል በማግኘቱ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በተለያየ ዘርፎች እያሳየች መሆኑን ተናግረዋል፡፡