Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ልማት ባንክ ኢትዮጵያ በግብርና እና በውሃ ዘርፍ ያላትን ሃብት እንድታለማ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ልማት ባንክ ኢትዮጵያ በግብርና እና በውሃ ዘርፍ ያላትን ሃብት ለማልማትና ለማሳደግ የምትደርገውን ጥርት እንደሚደግፍ የባንኩ የግብርና፣ የሰው ሀብት እና ማህበራዊ ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ገለጹ።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመረታ ሰዋሰው ከአፍሪካ ልማት ባንክ የግብርና የሰው ሀብት እና ማህበራዊ ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ቤት ደንፎርድ ጋር በጋና ተወያይተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ በንግግራቸው ፥ የግብርና ልማት በኢትዮጵያ መንግስት ቀዳሚና ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ለዚህ ማሳያ የሚሆነው መንግስት ለዘርፉ ካለው አገራዊ በጀቱ ከ10 በመቶ በላይ በቋሚነት በመመደብ ከአጠቃላይ የአፍሪካ ግብርና ልማት ፕሮግራም የመንግስት ወጪ በላይ ለዘርፉ በጀት በመመደብ ለግብርና ልማት ያለውን ቁርጠኝነት አሳይቷል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በግብርና ኤክስቴንሽን፣ በገጠር መሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ በግብርና ግብዓት አቅርቦት፣ በተፈጥሮ ሃብት አያያዝና በሴፍቲኔት ፕሮግራሞች በሰፊው ኢንቨስት ማድረጓንም ነው ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ።

ሆኖም ዘርፉ ለብዙ አደጋዎች የተጋለጠ በመሆኑ የተጠበቀው ደረጃ ላይ መድረስ እንዳልተቻለ ገልጸው ፥ ኢትዮጵያ ለግብርናው ዘርፍ የመደበችውን ሃብት ተጠቅማ በመካሄድ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች በጥሩ ሁኔታ እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

ከአፍሪካ ልማት ባንክ የግብርና፣ የሰውና ማህበራዊ ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት በበኩላቸው ፥ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ባንኩ ለኢትዮጵያ በተለይም ለእርሻና ውሃ ሴክተር ልማት ያላትን ሃብት ለማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

ቡድኑ በመካሄድ ላይ ያለው የምርታማነት ማሳደጊያ ፕሮጀክትና በቅርቡ የሚካሄደው የምግብ ዋስትና፣ የቦረና ውሃ አቅርቦት ፕሮጀክትና የደረቅ መሬት ስንዴ ልማት መርሐ ግብር ማሳካት በሚቻልበት ላይ መምከራቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.