Fana: At a Speed of Life!

የሀገርን ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ ሕገ ወጥ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ሚኒስቴሩ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገርን ብሄራዊ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ ሕገ ወጥ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አሳሰበ፡፡
ከሀገርና ሕዝብ ተጠቃሚነት በተጻረረ መልኩ የግል ጥቅማቸውን ብቻ ለማረጋገጥ ጥረት የሚያደርጉ ሕገ ወጥ አካላት መበራከታቸውን የገለጸው ሚኒስቴሩ÷ ይህም በሀገሪቱ የተረጋጋ የኢኮኖሚ ፍሰት እንዳይኖር አድርጓል ብሏል፡፡
ሚኒስቴሩ የግብይት ስርዓቱን ዘመናዊ እና በውድድር ላይ የተመሰረተ በማድረግ የሀገሪቱን እና የሕዝቡን አንጻራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም ገልጿል፡፡
መንግስት እየተስተዋለ ያለው የሸቀጦች ዋጋ ንረት በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ በሚገኙ ዜጎች ላይ የሚፈጥረውን ጫና ለማቃለል መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦችን ከውጪ በፍራንኮ ቫሉታ እና ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ ማድረጉን የገለጸው ሚኒስቴሩ÷ በዚህ መንገድ የሚገቡት ምርቶች ግን ለታለመላቸው ዓላማ ከመዋል ይልቅ ለተወሰኑ ሕገ ወጥ አካላት የኪስ ማድለቢያ ሲሆኑ ይስተዋላል ብሏል፡፡
ይህንን ያልተገባ ድርጊት ለማስቆም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተለያዩ የአሰራር ስርዓቶችን በመዘርጋት ላይ ሲሆን÷ የዚህ ሕገ ወጥነት ተዋንያን የሆኑ አካላት ከወዲሁ ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
በአሁኑ ወቅት ለተከሰተው የኑሮ ውድነት አንደኛው መንስኤ የግብይት ስርዓታችን የተራዘመ መሆኑ ነው ያለው ሚኒስቴሩ÷ ይህም አምራቾችና ሸማቾችን ሳይሆኑ በግብይት ሂደቱ ውስጥ ምንም እሴት የማይጨምሩ አካላት ብቻ ተጠቃሚ የሚሆኑበት አግባብ በመሆኑ ለኑሮ ውድነቱ መባባስ መንስኤ ሆኗል ማለቱን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.