Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በማዕድን ዘርፍ ከ458 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በማዕድን ዘርፍ ከ458 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ገለጹ።
የማዕድን ሚኒስቴር የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል።
የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ ለምክር ቤቱ የተቋማቸውን የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት÷ በተጠቀሰው ጊዜ ከማዕድን ዘርፍ ከ458 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።
ገቢው የተገኘው ከወርቅ፣ ጌጣጌጥና ኢንዱስትሪ ማዕድናት መሆኑን አመልክተዋል።
የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ባቀረቡት ሪፖርት÷ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የውጭ ንግድን በማሳደግ፣ የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት መደላድል መፍጠር እና የስራ ዕድል ፈጠራ ሥራዎች ላይ አበረታች ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል፡፡
የወርቅ ማዕድን ባለፉት ዘጠኝ ወራት 6 ሺህ 947 ኪሎግራም ተመርቶ ለብሄራዊ ባንክ የቀረበ ሲሆን÷ ይህም ከተያዘው ዕቅድ አንጻር 106 በመቶ አፈጻጸም ማሳየቱን እና ከ2013 ዓ.ም ጋር ሲነጻጸርም የ12 በመቶ ብልጫ አለው ብለዋል፡፡
የጌጣጌጥ ማዕድናትን በተመለከተም 2 ሺህ 317 ኪሎ ግራም ለውጭ ገበያ የቀረበ ሲሆን÷ ከዕቅዱ አንጻርም የ 103 በመቶ አፈጻጸም ማሳየቱን ኢንጂነር ታከለ ለምክርቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት ገልጸዋል፡፡

ማዕድን ሚኒስቴር ባለፉት ዘጠኝ ወራት ያስመዘገባቸው ውጤቶች አስቸጋሪ በሆነ ሀገራዊ እና ለዘርፉ ፈታኝ በሆነ ሁኔታ ውስጥ መሆኑም በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

በተለይም የዘርፉ የስራ ሁኔታ ለፀጥታ ስጋትና ችግሮች ቀጥተኛ ተጋላጭ በመሆኑ÷ በአብዛኛው የማዕድን ምርት ባለባቸው አካባቢዎችና ኩባንያዎች በከፊልና ሙሉ በሙሉ ምርት እንዲያቆሙ መደረጋቸውም ተገልጿል፡፡

ያም ሆኖ የወጪ ንግድ ማዕድናትን የምርት መጠን ለማሳደግ ልዩ የድጋፍ፣ የክትትልና የቁጥጥር ስርዓት በተመረጡ አካባቢዎች በመተግበሩ÷ አፈፃፀሙን ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት የተሻለ ማድረግ ተችሏል ነው የተባለው።

በአመለወርቅ ደምሰው
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.