Fana: At a Speed of Life!

በፋርማሲዩቲካል ዘርፍ ለሚሰማሩ የውጭ ኩባንያዎች የተመቻቹ የገበያ አማራጭ ዕድሎች አሉ – አምባሳደር ዳዋኖ ከድር

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በፋርማሲዩቲካል ዘርፍ ለሚሰማሩ የውጭ ኩባንያዎች ለብቻ ተለይተው ከተዘጋጁ ቦታዎች ጀምሮ የተመቻቸ የገበያ አማራጭ ዕድሎች መኖራቸውን አምባሳደር ዳዋኖ ከድር ለቻይና የኩባንያ ኃላፊዎች አስረዱ።

በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል የሚሲዮኑ መሪ የሆኑት አምባሳደር ዳዋኖ ከድር በቻይና ከሚገኙ 100 ትላልቅ የፋርማሴዩቲካል ኩባንያዎች መካከል አንዱ ከሆነው ሳውዝ ዌስት ፋርማሲውቲካል ኩባንያ በኢትዮጵያ መሰማራት በሚችልበት ሁኔታ ላይ መከረዋል፡፡

አምባሳደር ዳዋኖ ከድር ከኩባንያው ዋና ዳይሬክተር ከሆኑት ያ ዢያን ጋር በበይነመረብ ውይይት ያደረጉ ሲሆን፥ የኢትዮጵያ መንግስት በተለይ ለፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪው ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዘርፉ ለሚሰማሩ የውጭ ኩባንያዎች ለብቻ ተለይተው ከተዘጋጁ ቦታዎች ጀምሮ የተመቻቸ የገበያ አማራጭ ዕድሎች ያሉ መሆኑንም አምባሳደሩ አስረድተዋል።

አክለውም በኢትዮጵያ የቅድመ ኢንቨስትመንት ጉብኝት በማካሄድ ኢትዮጵያ ያላትን የገበያ አማራጭ በአካል እንዲመለከቱ ጥሪ አቅርበው ፥ አስፈላጊ በሆነው ሁሉ የሚሲዮኑ ድጋፍ እንደማይለያቸውም አረጋግጠዋል።

የኩባንያው ኃላፊ ስለቀረበላቸው ሰፊ ማብራሪያ አመስግነው ፥ በቀጣይ ከኩባንያቸው የተውጣጣ ከፍተኛ የልዑካን ቡድንን መርተው በኢትዮጵያ የቅድመ ኢንቨስትመንት ጉብኝት እንደሚያካሂዱ መናገራቸውን በቤጂንግ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.