በኢትዮጵያ ተከስተው ከነበሩ ግጭቶች ጀርባ የአሸባሪው ህወሓት እጅ መኖሩ በምርመራ ተረጋግጧል – ፍትሕ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ተከስተው ከነበሩ ግጭቶች ጀርባ የአሸባሪውህወሓት እጅ እንዳለበት በምርመራ መረጋገጡን ፍትሕ ሚኒስቴር ገለጸ።
በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች የግጭትና አለመረጋጋት ክስተቶች መስተዋላቸው ይታወቃል።
በተለያዩ ምክንያቶች በተከሰቱት ግጭቶች የበርካታ ወገኖች ህይወት ሲያልፍ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና መፈናቀልም ተከስቷል።
በእነዚህ ወንጀሎች ላይ ተሳታፊ የነበሩ አካላት በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑና ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ፍትሕ እንዲያገኙ መሰራቱን ፍትሕ ሚኒስቴር ገልጿል።
የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ፍቃዱ ጸጋ÷ በተለያዩ አካባቢዎች የነበሩ ግጭቶችን መንስኤ ለማጣራትና ወንጀለኞችን ተጠያቂ ለማድረግ በተደረገው ምርመራ የአሸባሪው ህወሓት የጥፋት እጆች መኖራቸው ተረጋግጧል ብለዋል።
አሸባሪው ህወሓት ግጭቶችን በጦር መሳሪያና በበጀት በመደገፍ እንዲሁም ስምሪት በመስጠት ስለመሳተፉ በመረጃና ማስረጃ ተረጋግጧል ነው ያሉት።
”እኔ ያልመራኋት አገር መቀጠል የለባትም” ብሎ የተነሳው አሸባሪ ቡድን አገር ለማፈራረስ የተለያዩ የጥፋት አማራጮች መጠቀሙን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።
የፍትሕ ሚኒስቴር ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በቴፒ፣ በቡራዩና በአዲስ አበባ፣ በአሶሳ እና ሌሎችም አካባቢዎች የተፈፀሙ ወንጀሎች ተጣርተውና ምርመራ ተደርጎባቸው ውሳኔ እንዲያገኙ ማስቻሉንም ነው የገለጹት።
በጌዲዮና ጉጂ እንዲሁም በሀዋሳ በተፈጠሩ ግጭቶች የወንጀሉ ተሳታፊ የነበሩ አካላትም የፍርድ ውሳኔ እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።
መነሻቸውን የሃይማኖትና የወሰን ጉዳይ አድርገው በቅርቡ የተከሰቱ ወንጀሎችን የሚመረምር ቡድን ወደ ስፍራው መላኩን ጠቅሰዋል።
በጎንደር፣ በደባርቅና በወራቤ ሃይማኖትን ሽፋን ያደረጉ እንዲሁም በጂንካና ደራሼ ወሰንን መነሻ አድርገው የተከሰቱ ግጭቶችን በማጣራት ወንጀለኞችን ተጠያቂ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች ሃይማኖትንና ብሔርን መነሻ አድርገው የተከሰቱ ግጭቶች በፌዴራል መንግስት ብቻ እንዲታዩ መወሰኑንም ተናግረዋል።
በቀጣይም የድንበርና የወሰን ጉዳዮችን በሕጋዊ መንገድ ለመፍታት ይሰራል ብለዋል።
የጥፋት ኃይሎች አገር የማፍረስ እንቅስቃሴ አሁንም የቀጠለ ቢሆንም÷ መንግስት ወንጀለኞችን ተጠያቂ የማድረግና የሕግ የበላይነትን የማስከበር ስራ አጠናክሮ ቀጥሏል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡