ተማሪዎች ዘንድሮ እንደሚደግሙ የሚናፈሰው ወሬ ከእውነት የራቀ ነው- የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ተማሪዎች “ዘንድሮ በያላችሁበት ክፍል ትደግማላቸሁ” በሚል የሚናፈሰው ወሬ ከእውነት የራቀ መሆኑን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡
በ2014 የትምህርት ዘመን ማጠቃለያ ላይ ተማሪዎች ለትምህርታቸው ትኩረት ሰጥተው ማጠቃለያ ፈተናዎችን ለመውስድ እየተዘጋጁ ባለበት በአሁኑ ወቅት÷ ማህበራዊ ኃላፊነት በጎደላቸው አካላት ሆን ተብሎ ተማሪዎችን ለማዘናጋት በዘንድሮ ዓመት ከክፍል ወደ ክፍል መዘዋወር የለም ተብሎ በማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች የሚናፈሰው ወሬ ፍፁም ከእውነት የራቀ መሆኑን ቢሮው አስታውቋል፡፡
ቢሮው የትምህርት ባለድርሻ አካላት “ተማሪዎች ዘንድሮ በያላችሁበት ትደግማላቸሁ” በሚል አሉባልታ ሳይዘናጉ ለትምህርታቸው ትኩረት ሰጥተው ለተሻለ ውጤት እንዲተጉ አሳስቧል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2014 የትምህርት ዘመን በከተማው የሚሰጠው ትምህርት ውጤታማ እንዲሆን ዘርፈ ብዙ ተግባራት በማከናወን ላይ መሆኑን የገለጸው ቢሮው÷ የበኩላቸውን ሚና ለተወጡ አካላትም ምስጋና ማቅረቡን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ የትምህርት ሚኒስቴር ባስተላለፈው መልዕክት፥ “ሁሉም የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ባሉበት የትምህርት ደረጃ እንዲቀጥሉ ተወስኗል” በሚል በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች የትምህርት ሚኒስቴርን ስም እና አርማ በመጠቀም የሚሰራጩት መረጃዎች ሀሰተኛ መሆናቸውን ገልጿል።
ስለሆነም ተማሪዎች የሚሰራጩት መረጃዎች የተሳሳቱ እና ከእውነት የራቁ መሆናቸውን አውቃችሁ ትኩረታችሁን ትምህርታችሁ ላይ ብቻ እንድታደርጉ እንጠይቃለን ብሏል።