Fana: At a Speed of Life!

በጣልያንና ፈረንሳይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጣልያንና ፈረንሳይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ፡፡

በሮም ከተማ ወጣቶችና በሚላኖ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ማህበር በሉምባርዲያ አስተባባሪነት በተዘጋጁ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች ያሰባሰቡትን ከ20 ሺህ ዩሮ በላይ በኢትዮጵያ በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች እንዲውል በጣሊያን ለኢትዮጵያ ኤምባሲ አስረክበዋል፡፡

ኤምባሲው ለተደረገው ድጋፍ አመስግኖ፥ ኤምባሲው ያሰባሰባውን የገንዘብ፣ የህክምና ቁሳቁሶችና አምቡላሶችን ወደ ኢትዮጵያ መላኩን ገልጿል። ድጋፉም በጤና ሚኒስቴር በኩል ለተጎዱት ወገኖች እንዲከፋፈል ተደርጓል ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያውያኑ ተመሳሳይ ድጋፎችን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ኤምባሲው ጥሪ አቅርቧል፡፡

በተመሳሳይ በፈረንሳይ አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ለተፈናቀሉ ወገኖች እንዲሁም በጦርነት ጉዳት ለደረሰበት ኮምቦልቻ ጠቅላላ ሆስፒታል ድጋፍ አድርገዋል።

ድጋፉ፥ በደብረ ብርሃን ከተማ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ 1 ሺህ ያህል ወገኖች መከፋፈሉም ተገልጿል፡፡

በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰበት የኮምቦልቻ ጠቅላላ ሆስፒታልም 6 ሺህ ዩሮ ግምት ያላቸው መድሃኒቶችንና የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጉን በፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.