በአገር አቀፍ ደረጃ በተመረጡ 36 ሆስፒታሎች ችግር ፈቺ የሆኑ አዳዲስ አሰራሮች ሊተገበሩ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአገር አቀፍ ደረጃ በተመረጡ 36 ሆስፒታሎች ችግር ፈቺ የሆኑ አዳዲስ አሰራሮች ሊተገበሩ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ አዳዲስ አሰራሮችን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እና በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ ተገኝተው አስጀምረዋል፡፡
በአዲስ አበባ በሁሉም የመንግስት ሆስፒታሎች እና በሁሉም ክልሎች በተመረጡ ሆስፒታሎች 4 ዋና ዋና ተግባራት የሚተገበሩ ሲሆን÷ በአገልግሎት አሰጣጥ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ተጠያቂነት፣ በሃብት አጠቃቀምና ቅንጅታዊ አሰራሮች ተግባራዊ እንደሚደረጉ ዶ/ር አየለ ተሾመ ተናግረዋል።
በመድረኩ በየሆስፒታሎቹ የሚሰጡ አገልግሎቶች ተጠያቂነት ፣መረጃዎችን መሰረት ያደረጉ ለተገልጋይ ቅድሚያ፣ አስተማማኝና ውጤታማ የሆነ አገልግሎት መስጠት፣ በየተቋማቱ ያለውን የሰው እና የቁሳቁስ ሃብቶችን በአግባቡ መጠቀም እና ቅንጅታዊ አሰራርሮች ተግባራዊ በማድረግ በተገልጋይ እና በባለሙያዎች በኩል የሚነሱ ቅሬታዎች መፍትሄ ያገኛሉ ብለዋል።
በድንገተኛ ህክምና፣ በተኝቶ ህክምና፣ በተመላላሽ ህክምና፣ በመድሃኒት አቅርቦት፣ በላብራቶሪ እና በኢሜጅግ አገልግሎት እንዲሁም በሌሎች ክፍሎች ላይ አራቱ አንኳር ተግባራት ተግባራዊ የሚደረጉ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ሆስፒታሎቹ ለተገልጋይ በሚሰጡት አገልግሎት ይመዘናሉ፤ የተሻላ አፈፃፀም ያስመዘገቡ ሆስፒታሎችንም እውቅና በመስጠት ይበረታታሉ መባሉን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡