Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለአፈር ማዳበሪያ ግዥ ከ50 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን አስታወቀ

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለ2014/15 ዓ.ም የምርት ዘመን ለአፈር ማዳበሪያ ግዥ ከ50 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን አስታውቋል።

መንግስት የግብርና ዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ ሰፊ ዕቅድ ይዞ እየሰራ ሲሆን÷ ይህን እውን ለማድረግም የአፈር ማዳበሪያን ጨምሮ የግብርና ግብዓቶችን ማሟላት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ተብሏል፡፡

በተለይ ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም ጂኦ-ፖለቲካ ምክንያት እየተፈተነ ያለውን የማዳበሪያ አቅርቦት ችግር ለመፍታት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ እንደገለጹት÷ ባንኩ በአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት ምክንያት በግብርናው ዘርፍ የተያዘው አገራዊ እቅድ እንዳይስተጓጉል ትልቅ ስራ ሰርቷል።

የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ዓለምን የፈተነ የዋጋ ንረት ማስከተሉን ጠቅሰው÷ ከፍተኛ የማዳበሪያ አምራች የሆኑት የሁለቱ አገሮች ግጭት የአፈር ማዳበሪያ ዋጋና አቅርቦት ላይ ተግዳሮት መፍጠሩን ተናግረዋል።

ሌሎች የአፈር ማዳበሪያ አምራች አገራትም በጦርነቱ ምክንያት ምርታቸውን ለገበያ በማቅረብ ረገድ ችግር እንደገጠማቸው ገልጸዋል።

ከጦርነቱ በፊት 700 ዶላር ይሸጥ የነበረው የአንድ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ጦርነቱ እንደተጀመረ ከእጥፍ በላይ መጨመሩን ጠቁመው÷አሁን ላይ ያለው የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር እስከ አራት እጥፍ ጭማሪ ማሳየቱን አንስተዋል።

ባንኩ ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ ከሚያደርግባቸው ዘርፎች አንዱ ግብርና መሆኑን የገለጹት የባንኩ ፕሬዚዳንት÷የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ትልቅ ድርሻ እንደሚይዝ ተናግረዋል።

የአፈር ማዳበሪያ አቅራቢ አገራት እንደ ከዚህ ቀደሙ በዱቤ ለመሸጥ አለመፈለጋቸው ትልቅ ፈተና ነበር መለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ቢጨምርም ከዚህ የሚቀድም አንገብጋቢ ጉዳይ ባለመኖሩ ለሌሎች ዘርፎች ሊውል የነበረ ገንዘብ ጭምር ወደ ግብርናው እንዲዞር መደረጉን ተናግረዋል።

በከፍተኛ ጥረትና ርብርብ ከውጭ የተገዛው ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ መደረጉን ጠቅሰው÷በዚህ ረገድ በተለይ ብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ጠቁመዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.