Fana: At a Speed of Life!

ሀገራዊ ለውጡ ተቋማዊ ሆኖ እንዲቀጥል ተባብሮ መስራት እንደሚገባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ላለፉት 6 ቀናት “አዲስ ፖለቲካዊ ዕይታ አዲስ ሀገራዊ እምርታ” በሚል ለከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች ሲሰጥ የነበረው የስልጠና መድረክ በዛሬው ዕለት ተጠናቋል።
 
በማጠቃለያ መድረኩ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፥ ሀገራዊ የለውጡ ሂደት ፈታኝ ቢሆንም ፈተናውን ለማለፍ በጥበብ እና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የአመራር ዘይቤ በመከተል ዛሬ ላይ መድረስ መቻሉን ከዚህ ስልጠና አመራሩ ግንዛቤ ማግኘቱን ገልጸዋል።
 
በለውጡ ሂደት ተስፋን የሚጭሩ ትላልቅ ስራዎች መሰራታቸው በተለይም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የደህንነት፣ የሰላምና የጸጥታ ተቋሞች ላይ የተደረጉ መሰረታዊ ሪፎርሞች በጊዜያዊነት ብቻ ሳይሆን ለሀገራዊ ግንባታው ወሳኝ የሆነ ሚና እንዲጫወቱ ማስቻል የተሰራውን ስራ ሰልጣኙ በተግባር ጭምር እየተመለከተ የሰለጠነበት ሁኔታ እንደነበርም አንስተዋል።
 
አጠቃላይ ስልጠናው በአመራር የመሪነት ሚና ላይ ያተኮረ እንደነበር የገለጹት ከንቲባዋ÷የተቋም ግንባታ፣ ተቋማዊ አሰራሮች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውና ሀገራዊ ለውጡ ተቋማዊ ሆኖ እንዲቀጥል ሁሉም ተባብሮ መስራት እንደሚገባው አመላክተዋል።
 
የፓርቲ ተቋማዊ ግንባታ ለመንግስትና ለሀገራዊ ጥንካሬ ወሳኝ ነው፤ ጠንካራ መንግስት የሚኖረን እና ጠንካራ ሀገር የምንገነባው በጠንካራ ፓርቲ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
 
ከንቲባ አዳነች በየደረጃው ያለው አመራር ተግባርን አቀናጅቶ መምራት ይገባዋል ማለታቸውን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.