Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮ-ቱርክ የኢንቨስትመንት ፎረም በቱርክ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቱርክ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከአዳና ቻምበር ኦፍ ፎረም እና ከአዳና ቆንስላ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት እድል የሚያስተዋውቅ ፎረም በቱርክ አዳና ከተማ ተካሂዷል።

በፎረሙ በቱርክ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ ባለሃብቶች እንዲሁም የሦስት ከተሞች የክብር ቆንስላዎች ተሳትፈዋል።

የአዳና ከተማ የንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቲላ ሜኔቭስ መሰል ፎረም ከኤምባሲው ጋር በጋራ መዘጋጀቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነትን የበለጠ ለማሳደግ እንደሚረዳ ተናግረዋል።

በአዳና የኢትዮጵያ የክብር ቆንስል ዩሱፍ ካን ÷ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለውን የንግድ እና ኢንቨስትመንት ሁኔታ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ነው የገለጹት::

በቱርክ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አደም መሀመድ ባደረጉት ንግግር፥ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በኢንቨስትመንት፣ በንግድና በፖለቲካ ዘርፎች በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን በመግለጽ ስምምነቶቹን ወደ ተግባር ለመቀየር በትብብር መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም የኢትዮጵያን የንግድ እና የኢንቨስትመንት ምቹ አማራጮችን እንዲጠቀሙ ለቱርክ ባለሃብቶች ጥሪ አቅርበዋል።

የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ኔሜ በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ ስላለው ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ፣ ስለተደረጉ የኢንቨስትመንት ማሻሻያዎች፣ የትኩረት መስኮች ፣ ያሉ ማበረታቻዎች እና እድሎች አስረድተዋል::

በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ለሚፈልጉ የቱርክ ባለሀብቶች ሁሉ ፅ/ቤታቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ መግለፃቸውን ከአንካራ የኢትዮጵያ ኤንባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.