በሽታን መከላከልና ጤናን ማበልጸግ መሰረት ያደረገ ፖሊሲ በመተግበሩ አበረታች ውጤት መመዝገቡ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በሽታን መከላከልና ጤናን ማበልጸግ መሰረት ያደረገ ፖሊሲ ተግራዊ እያደረገች በመሆኗ በሽታዎችን በመከላከልና በመቆጣጠር አበረታች ውጤት መመዝገቡን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ ተናገሩ፡፡
ከ22 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ሰዎችን በስነ ተዋልዶ ጤና፣ በስርዓተ ጾታ እና በቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ዙርያ ተጠቃሚ በሚያደርግ ፕሮጀክት ላይ የትግበራ አካላት አውደ-ጥናት ተካሄደ፡፡
ፕሮጀክቱ ከኮሪያ ዓለምአቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ኮይካ) በተገኘ 3 ነጥብ 4 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ የሚተገበር ሲሆን ÷በኢትዮጵያ ውስጥ የተመጠነ፣ ደስተኛ እና ውጤታማ የሆነ ቤተሰብ ፕሮጀክት ሁለተኛው ክፍል በፈረንጆቹ ከ2019 እስከ 2024 ድረስ ተግባራዊ የሚሆን ነው ተብሏል።
በዚህ አውደ ጥናት ላይ የጤና ሚኒስተር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ ÷ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ጤና ማበልጸግና በሽታ መከላከልን መሰረት ያደረገ ፖሊሲ ተግራዊ እያደረገች በመሆኗ ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑበሽታዎችን በመከላከልና በመቆጣጠር፣ የእናቶችንና የህጻናት ጤና በማሻሻል፣ የህመምና የሞት ምጣኔን በመቀነስ፣ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተጠቃሚነትን ከማስፋት እና በሌሎች ዋና ዋና የጤና ፕሮግራሞች ላይም አበረታችና ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል፡፡
ዶክተር ደረጀ የዚህ ፕሮጀክት ትግበራ ለሁለተኛው የጤናው ዘርፍ የትራንስፎርሜሽ ዕቅድ ግቦች ውጤታማነት ያግዛል ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ፕሮጀክቱ ስነ-ተዋልዶ ጤና እና ስርዓተ ጾታ ላይ የተሻለ ግንዛቤ እንዲፈጠር በማድረግ እንደዚሁም የእናቶች ሞት ምጣኔ እና ያልተመጠነ ቤተሰብ እንዲቀንስ ከማስቻል አኳያ ሚና እንደሚኖረው ተናገረው ለተግበራዊነቱም በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ትብብር እንዲያደርጉ ሚኒስትር ዴኤታው ጠይቀዋል፡፡