እስካሁን 28 ሺህ ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ ዓረብያ ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ሁለት ወራት በሳውዲ ዓረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 28 ሺህ ዜጎች ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በሳውዲ ዓረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ በእስር ቤቶችና በማቆያ ማዕከላት ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሃገር ቤት ለመመለስ ብሄራዊ ኮሚቴ በማቋቋም መጋቢት 21 ቀን 2014ዓ.ም ነው የመመለሱ ስራ የተጀመረው።
ባላለፉት ሁለት ወራት በሳምንት ዘጠኝ ጊዜ በሚደረጉ የአውሮኘላን በረራዎች ዜጎችን መመለሱ ሳይቋረጥ የቀጠለ ሲሆን ፥ በዚህም እስካሁን ድረስ በድምሩ 28 ሺህ ያህል ዜጎችን መመለስ መቻሉን ተገልጿል።
በሳውዲ ዓረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ በእስር ቤቶች እና በማቆያ ማዕከላት ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሃገር ቤት ለመመለስ እስካሁን የተከናወኑ ተግባራት ሪፓርት የቀረበ ሲሆን ፥ ያጋጠሙ ችግሮች እና ቀጣይ ስራዎችን አስመልክቶም ብሄራዊ ፈፃሚ ኮሚቴው ዛሬ ውይይት አካሂዷል።
በቀረበው ሪፓርት ላይ እንደተመለከተው፥ እስከ ግንቦት 17 ቀን 2014 ዓም ድረስ ለሃገራቸው ከበቁ ተመላሾቹ መካከል ወንዶች 18 ሺህ 676 ሲሆኑ ፥ ሴቶች ደግሞ 9 ሺህ 308 ናቸው።
ለተመላሾቹ ዘጠኝ የማቆያ ማዕከላት በአዲስ አበባ ተዘጋጅተው አገልግሎት እየሰጡ እንዲገኙም ተገልጿል።
መኝታ፣ አልባሳት፣ የምግብና መጠጥ አቅርቦት ፣የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ፣ የህክምና፣ የምክር የስልክና መሰል አገልግሎትች እየቀረበላቸው እንደሆነም የቀረበው ሪፓርት ያመለክታል።
የብሄራዊ ፈፃሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በዚህ ወቅት እንዳሉት ፥ ዜጎችን የመመለሱ ስራ ከጀመረበት ዕለት እስካሁን በታቀደው መሰረት ሳይቋረጥ መቀጠሉን ገልፀዋል።
ለዚህም በውጤት መገኘት በስራው እየተሳተፉ ያሉ ተቋማት ቅንጅታዊ ስራ አንዱ ምክንያት እንደሆነም ነው አምባሳደር ብርቱካን የተናገሩት።
ከሰባት እስከ 11 ወራት ውስጥ 100ሺህ ዜጎችን የመመለስ እቅድ መያዙን አስታውሰው ፥ በቀሪ ጊዜም የተጠናከረ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
አምባሳደር ብርቱካን ጨምረውም ፥ የዜጋ ተኮር ዲኘሎማሲ የመንግስት ዋንኛ ትኩረት ሆኖ እንደሚቀጥል ገልፀው፥ በቀጣይም በታንዛኒያ፣ ሱዳን፣ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣የመን እና ኦማን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ዜጎችን የመመለስ ስራ ለመጀመር ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በቀጣይ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ዘመቻ የሚሳተፉ አካላት ርብርባቸውን እንዲያጠናክሩ ሌሎች ባለድርሻዎችም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በሲስተም የታገዘ የመረጃ አያያዝ ስርአት አለመኖር እንዲሁም ሴትና ወንድ ተመላሾችን በአንድ በረራ ማምጣት በማቆያ ማዕከላት አስተዳደር ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑ በሪፖርቱ ላይ ተነስቷል።
ሰዎች እና ዕቃዎቻቸውን በተለያየ በረራዎች እንዲመጡ መደረጉ ደግሞ ተመላሾችን ወደ ቀያቸው በመሸኘቱ ሂደት ላይ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩም ተመላክቷል።
ዜጎችን ከመመለስ ባሻገር መልሶ ለማቋቋም የስራ ፈጠራ ስልጠና ለመስጠት የተያዙ እቅዶችን በመፈፀም ረገድ ክፍተት መኖሩ በተደረገው ውይይት ላይ ተነስቷል።
የበጀት እጥረትንና በሪፓርቱ የቀረቡ ችግሮችን በመቅረፍ በቀጣይ የተቀመጠውን እቅድ ለማሳካት እንደሚሰራም ተወያዮች መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።