Fana: At a Speed of Life!

የደቡብ ክልል የጸጥታ ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 19 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክር ቤቱ ከዚህ ቀደም የነበሩ የህዝብ ጥያቄዎችን መመለስ የሚያስችል ስርዓት በመዘርጋት በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በልዩ ትኩረት እንደሚሰራም ተጠቁሟል።

በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሀላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ በህብረተሰቡ እና በጸጥታ ሀይሉ ጥረት በርካታ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን መከላከል መቻሉን አብራርተዋል።

ሆኖም ግን በክልሉ አዳዲስ የጸጥታ ችግሮች መከሰታቸውንም ገልጸዋል

የተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት ልዩ እቅድ በማዘጋጀት የክልሉ የጸጥታ ምክርቤት ውሳኔዎችን ማሳለፉን ጠቁመዋል።

በክልሉ በርካታ የህዝብ ጥያቄዎች መኖራቸውን የተናገሩት ኃላፊው ከዚህ ውስጥ የአደረጃጀት ጥያቄ ተጠቃሽ ነው ብለዋል።

እነዚህን ጥያቄዎች መሪው ፓርቲ እና መንግስት ምላሽ የሚሰጥ ሆኖ ሳለ የህዝብን ጥያቄ በመጥለፍ ዜጎች እንዲሞቱ፣ እንዲፈናቀሉና የንብረት ውድመት እንዲደርስ ምክንያት የሆኑ አካላት መኖራቸውን አስረድተዋል።

የአደረጃጀት ጥያቄዎች ህዝብን በማወያየት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲፈቱ አቅጣጫ መቀመጡን አቶ አለማየሁ አብራርተዋል።

ከዛሬ ጀምሮ የአደረጃጀት ጥያቄን ሽፋን በማድረግ በህዝብ ላይ ጉዳት በሚያደርሱ አካላት ላይ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ውሳኔ መተላለፉንም ገልጸዋል።

በክልሉ ሁሉንም አካባቢ ለማተራመስ የኢመደበኛ አደረጃጀት እንዳለ የገለጹት ኃላፊው በወጣት፣ በምሁራን እና በአካባቢ ሽማግሌዎች ስም በመደራጀት የህዝቡን ጤናማ እንቅስቃሴ ለመገደብ ጥረት የሚያደርጉ አካላት መኖራቸውንም ተናግረዋል።

በግምገማ መድረኩ እንደተመላከተው አመራሩ የተከሰቱ የጸጥታ ችግሮች አስተባብሯል፣ አቀናጅቷል እንዲሁም ባለቤት ሆኖ መርቷል።

ለአብነትም ደራሼን፣ደቡብ ኦሞን፣አሌ እና ኮንሶን በመጥቀስ በእነዚህ አካባቢዎች በህዝብ ውስጥ የሚነሱ ጉዳዮችን ለአጥፊዎች ግብአት በሚሆን መንገድ አመራሩ አደራጅቶ አካባቢው የትርምስ ቀጠና እንዲሆን መነሻ መሆኑንም ነው የገለጹት።

አያይዘውም የጸጥታ አካሉ ገለልተኛ ሆኖ ህግ ከማስከበር ይልቅ በድርጊቱ መሳተፉን ጠቅሰው፥ በተፈጠረው ችግር ተሳትፎ ባደረጉ አመራሮች እና የጸጥታ ሀይሎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ጠቁመዋል።

በክልሉ ሀገር ለማፍረስ ሀሰተኛ የማህበራዊ ትስስር ገጾች በግለሰብ እና በቡድን በመክፈት ህዝብና መንግስትን ለማጋጨት እየሰሩ ያሉ አካላት ላይ በተደራጀ መንገድ እርምጃ የሚወሰድ ሲሆን ከዚህ በፊት ባሰራጩት መረጃ ልክ የደረሰውን ጉዳት በመፈተሽ እርምጃ እንደሚወሰድም ነው የተናገሩት።

ታጥቀው ጫካ የገቡ ሀይሎች በተገቢው መንገድ እጅ እንዲሰጡ ይጠየቃሉ ያሉት ኃላፊው ነገር ግን የህዝብን ሰላም ለማወክ በተግባራቸው በሚቀጥሉት ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወሰድም አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል።

በቤተ እምነቶች መካከል ጥርጣሬ እንዲኖር እና የህዝቦችን አንድነት በሚፈታተኑ አካላት ላይም እርምጃ ይወሰዳል ነው ያሉት።

በተስፋዬ መኮንን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.