የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር በማህበር ለተደራጁ የመኖሪያ ቤት ህብረት ሥራ ማህበራት ቦታ ማስረከብ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ግንት 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር በማኅበር ለተደራጁ የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት ቦታ ማስረከብ መጀመሩን አስታወቀ።
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ በትግሉ ተስፋሁን በዚህ ዓመት በሁለት ዙር በማኅበር ለተደራጁ ማኅበራት ቦታ ለማስረከብ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
አሁኑ ሰዓትም በመጀመሪያው ዙር ለ196 ማኅበራት በመሸንቲ ሳይት ቦታ ርክክብ ተደርጓል ብለዋል፡፡
እስከ ግንቦት መጨረሻም ለተጨማሪ 469 የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት በዘንዘልማ ሳይት ቦታ ለመስጠት ከሶስተኛ ወገን መሬት ነጻ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
በሁለተኛ ዙርም ከተማ አስተዳደሩ ሁሉንም የተደራጁ ማኅበራት ቦታ ለማስረከብ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ማጠናቀቁን ገልጸዋል።
ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሠብ ክፍሎችም መጠለያ ያገኙ ዘንድ ከባለሀብቶችና ከተለያዩ አካላት ጋር ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
የእርሻ መሬታቸውን ለማኅበራቱ የሚለቁ አርሶአደሮችም ካሳ መከፈሉንና የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ መሠጠቱን ጠቅሰው፥ ለአቅመ አዳም የደረሱ የአርሶ አደር ልጆችም በ11ማኅበራት በማደራጀት የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ መሰጠቱን አስረድተዋል፡፡
ከተማው ካለው ውስን የመሬት ሀብት አኳያ ከዚህ በኋላ ሌሎች ማኅበራትን ለማስተናገድ አስቸጋሪ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው÷ የጋራ የመኖሪያ ቤት አፓርትመንት በመገንባት ነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለማድረግ ከክልሉ መንግስት አቅጣጫ እየጠበቁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በበላይነህ ዘለዓለም