ከሀምሌ እስከ ግንቦት ወር መጀመሪያ ድረስ ከ72 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ትግራይ ተልኳል-የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በበጀት ዓመቱ ከሀምሌ እስከ ግንቦት ወር መጀመሪያ ከ72 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ወደ ትግራይ ክልል መጓጓዙን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
መንግስት ወደ ትግራይ ክልል የሚላከው ሰብዓዊ ድጋፍ ሳይስተጓጎል እንዲጓጓዝ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ መቀጠሉንም ኮሚሽኑ አስታወቋል።
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ደበበ ዘውዴ እንደገለጹት÷ ኮሚሽኑ ከአጋር አካላትና ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር ወደ ትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ ሳይስተጓጎል እንዲላክ እያደረገ ነው፡፡
በዚህም በዋናነት ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች፣ ነዳጅና መድሃኒትን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎች ወደ ትግራይ ክልል መጓጓዙን ጠቁመዋል።
ከ2014 በጀት ዓመት መጀመሪያ ሀምሌ ወር እስከ ግንቦት ወር መጀመሪያ ባሉ ጊዜያት ከ72 ሺህ 485 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆነ ቁሳቁሶች ወደ ትግራይ ክልል መላኩንም ነው የገለጹት፡፡
ከዚህ ውስጥ 61 ሺህ 442 ሜትሪክ ቶን በላይ የምግብና የአልሚ ምግብ ድጋፍ በአፋር በኩል መጓጓዙን አብራርተዋል።
በተጨማሪም ከ11 ሺህ 43 ሜትሪክ ቶን በላይ የሚሆነው ደግሞ ውሃ፣ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ፣ አልባሳትና ሌሎች ድጋፎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ድጋፉም በተጠቀሱት ወራት በአጠቃላይ በ223 የአየር በረራ እና በ1 ሺህ 947 የጭነት ተሽከርካሪዎች የተጓጓዘ እንደሆነ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ድጋፉን ተደራሽ ለማድረግ 93 በሰብዓዊ ድጋፍ ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች መሳተፋቸውንም ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽኑ ከአጋር አካላትና ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር ወደ ትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ ሳይስተጓጎል እንዲደርስ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።