በኦሮሚያ ክልል የሥነ ምግባር ጉድለት ባሳዩ ከ18 ሺህ በላይ ሰራተኞች ላይ የእርምት እርምጃ ተወሰደ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 19 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ሕዝቡን በአግባቡ ማገልገል ባልቻሉና የሥነ ምግባር ጉድለት ባሳዩ ከ18 ሺህ በላይ ሰራተኞች ላይ የእርምት እርምጃ ተወሰደ።
በሰራተኞቹ ላይ የ20 ሚሊየን ብር የገንዘብ መቀጮን ጨምሮ ልዩ ልዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች መወሰዳቸውም ነው የተገለጸው።
የኦሮሚያ ክልል ሴክተር መስሪያ ቤቶች የአገልግሎት አሰጣጥና የአጭር ጊዜ ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በግምገማው ላይ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወሉ አብዲ የክልሉ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የስራ ሃላፊዎች እና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
አቶ አወሉ አብዲ ግምገማው ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ሕዝቡ የሚያነሳቸው ቅሬታዎች በምን መልኩ እየተፈቱ እንዳለ መገምገም፣ መልካም ተሞክሮዎችን ማስፋፋትና ሊቀረፉ ባልቻሉ ተግዳሮቶች ላይ የማስተካከያ እርምጃ የመውሰድ አላማ ያለው ነው ብለዋል።
እስካሁን ድረስ የሥነ ምግባር ጉድለት በታየባቸውና ሕብረተሰቡን በአግባቡ ማገልገል ባልቻሉ በዞን ደረጃ በ16 ሺህ ሠራተኞችና አመራሮች ላይ፣ በከተሞች ደረጃ ደግሞ በ1ሺህ 600 ሰራተኞችና አመራሮች ላይ እንዲሁም በክልል ደረጃ በ1 ሺህ 100 ሰራተኞች ላይ ከስራ የማሰናበትና የደመወዝ መቀጮን ጨምሮ ልዩ ልዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች መወሰዳቸውንም ገልጸዋል።
በተያያዘም የስራ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ለተወጡ ሴክተር መስሪያ ቤቶች በበጀት አመቱ ማጠቃለያ ላይ እውቅና እንደሚሰጥ መናገራቸውን ኦ ቢ ኤን ዘግቧል።