በህልውና ዘመቻው ለተሳተፉ የደቡብ ክልል የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት ማዕረግ የማልበስ መርሐ ግብር ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በህልውና ዘመቻው ለተሳተፉ የደቡብ ክልል ተመላሽ የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት ማዕረግ የማልበስ መርሐ ግብር በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሄደ፡፡
በመርሐ ግብሩ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳ፣ የደቡብ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ፣ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ፣ የዞንና በየደረጃው የሚገኝ የመንግስት የስራ አመራሮች እንዲሁም የዞኑ ነዋሪዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
አቶ እርስቱ ይርዳ ባደረጉት ንግግር ÷ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የተበረከተላቸውን ሽልማትና እውቅና እየተቀበሉ ሲሆን ፥ በህልውና ዘመቻው ላይ የተሰዉ አባላቶች የዘወትር ጀግኖች መናቸውን ገልጸዋል፡፡
በዘመቻው በተለያዩ ዓውደ ግንባሮች የተሰጣቸውን ግዳጅ በጀግንነት አኩሪ ታሪክ ሰርተዋል ያሉት አቶ እርስቱ ፥ የህዳሴ ግድብ ሳይደናቀፍ ግንባታው እንዲቀጥል ያበረከቱት ተጋድሎና ያሳዩት የሀገር ፍቅር እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
አክለውም አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን የማፍረስ ፍላጎቱ ዛሬም መቀጠሉን ገልፀው ፥ የትግራይን ህዝብ በእሳት ለመማገድ እየሰራ መሆነኑን ማወቅ አለበት ብለዋል፡፡
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አለማየሁ ማሞ ፥ የክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት በአገራዊ የህልውና ጥሪ ላይ በመሳተፍ ላስመዘገቡት ድል አመስግነው ፥ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ጥቃት ለማድረስ የሚሞክሩ አካላትን እኩይ ተግባር ማክሸፍን ጨምሮ በተሰማሩባቸው ግንባሮች ሁሉ የህይወት መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር ጠላትን ድል በመንሳት የጀግንነት ታሪክ መፈጸማቸውን ነው የገለጹት፡፡
በደራሼ ልዩ ወረዳም መስዋዕት የሆኑትን ስማቸው ከፍ ብሎ የሚነሳና በክብር እውቅና የሚሰጥ እንደሆነ ገልፀው ፥ በቀጣይም የሀገርን ሰላም የመጠበቁ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡
የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሀላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ ፥ የአሸባሪው የህወሓት ቡድን አገር ለማፍረስ ጥረት ቢያደርግም ሳይሳካለት መቅረቱን አንስተው ፥ ትናንት በጀግኖች ልጆቿ መስዋዕትነት ክብሯ ተጠብቆ ዛሬ ላይ ደርሳለችው ኢትዮጵያ፥ ወደፊትም በብርቱ ልጆቿ ክብሯ ተጠብቆ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በእውቅና አሰጣጥ እና ማዕረግ የማልበስ መርሐ ግብሩ ላይ በተለያየ ደረጃ የጀብድ ሜዳይ ተሸላሚዎች በክብር እውቅና፥ ሽልማትና ማበረታቻ ተበርክቶላቸዋል፡፡
በተለይም ልዩ ተሸላሚዎች የገንዘብ፣ የደረጃና የደመወዝ ዕድገት እንዲያገኙ መወሰኑም ተገልጿል፡፡
በሀገራዊ ግዳጅ ወቅት የህይወት መሰዋዕትነት የከፈሉ የክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት ቤተሰቦች የክብር እውቅና የተሰጣቸው ሲሆን ፥ የቤተሰብ አባላቱም ከርዕሰ መስተዳደሩ የማዕረግ እድገቱን ተቀብለዋል፡፡
በብርሃኑ በጋሻው በማስተዋል አሰፋ