Fana: At a Speed of Life!

ህግን በማስከበር ደረጃ መንግስት እየሠራ ያለውን ስራ እንደሚደግፉ የፓለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአካባቢን ሠላም በማስጠበቅና ህግን በማስከበር ደረጃ መንግስት እየሠራ ያለውን ስራ እንደሚደግፉ በደሴ ከተማ የሚገኙ ፓለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ፡፡

የደሴ ከተማ አስተዳደር ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር ምክክር ያካሄደ ሲሆን÷ የኢዜማ ፓርቲ ደሴ ቅርንጫፍ ሊቀመንበር አቶ አይነቱ ሀይሉ በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት፥ የመንግስት ቀዳሚው ተግባር ሠላምን ማስፈንና ህግን ማስከበር ነው፡፡

በከተማዋ ብሎም በክልል ደረጃ እየተሠራ ያለውን ሰላምንና ህግን የማስከበር ስራን እንደሚደግፉ ጠቅሰው÷ በቅድሚያ ግን ሰፊ ምክክርና ውይይት በየደረጃው ያስፈልግ እንደነበር አንስተዋል፡፡

ህግን የማስከበርና ሠላምን የማስፈን ስራ በመንግስት ብቻ የሚፈጸም ባለመሆኑ እንደ ክተት አዋጁ ሁሉ በሰላሙ ጉዳይም ማህበረሰቡ የመፍትሄ አካል እንዲሆን እድል ሊሠጥ ይገባ እንደነበርም ነው የገለጹት፡፡

አክለውም በከተማ ደረጃ እየተሠራ ያለው ስራ እንደሚያስመሰግን ገልጸው÷ እንደ ፓርቲም እንደ ከተማ ነዋሪም ህግን የማስከበር ስራው በጥንቃቄ የተመራ ነው ብለዋል፡፡

የኢዜማ ፓርቲ ደሴ ቅርንጫፍ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ሻምበል ደምሌ በበኩላቸው ፥ ለሠላምና ህግ መከበር ሁሉም ሰው ፍላጎትም እምነትም አለው ነው ያሉት፡፡

አሁንም እየተሠራ ያለውን ስራ በተሻለ መልኩ ለመፈፀም መግባባትን መፍጠር ወሳኝ አማራጭ መሆኑን ያመላከቱት ሃላፊው ፥ በከተማዋ ያለውን ሠላም የማስከበር ተግባር የበለጠ በህዝብ የተደገፈ እንዲሆን ምክክር ያስፈልጋል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

መደበኛ ያልሆኑ ቡድኖች ላይ ብቻ ሳይሆን በመደበኛ መዋቅር ውስጥም ያሉ ችግር ፈጣሪዎችን ማረምና ሰላምን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ አቶ ስዩም አበበ የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ተወካይ ናቸው፡፡

የእናት ፓርቲ ደሴ ቅርንጫፍ ስራ አስፈጻሚ አቶ ዳዊት አያሌው ፥ የሠላም ጉዳይ የማህበረሰብ አንድነትና ትበብር የሚጠይቅ ነው ያሉ ሲሆን ፥ እየተወሰደ ያለው ሠላም የማስከበር ሁኔታ ለህዝብ ጥቅም ታልሞ የተሠራ መሆኑን እንደሚያምኑ ጠቅሰዋል፡፡

አክለውም ÷ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን የጋራ መግባባት በየደረጃው ካሉ የህብረተሠብ ክፍሎች ጋር ያስፈልግ እንደነበር አንስተው ፥ በደሴ ከተማ እየተሠራ ያለው የሠከነና በበሳል አመራር ሰጭነት የተመራው ስራ ከተማዋን ሰላም ያደረገ ለቀጣይም አስተማሪ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ደሴ ቅርንጫፍ ሃላፊ አቶ ሞላ ሁሴን በበኩላቸው ፥ በደሴ ከተማ በምርጫና በህልውና ዘመቻው ላይ የነበረውን ትብብር አሁን ያለውን የማህበረሰቡን ሠላምና ደህንነት የማሥጠበቅ ሂደት በአብሮነት ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

ፓርቲዎች ግባቸው ልማትና ዴሞክራሲን ማምጣትና ህዝብን ተጠቃሚ ማድረግ ከሆነ ሰላም በማስከበር ረገድ ከጎናችን መሆን አለባቸው ያሉት ደግሞ የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ ናቸው፡፡

ከህዝቡም ከፖለቲካ ፓርቲዎችም የሚሠጡ አስተያየቶችን በመቀበል ህዝቡን የልማት የሠላምና የዴሞክራሲ ተጠቃሚ ለማድረግ እንሠራለንም ብለዋል፡፡

በአለባቸው አባተ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.