Fana: At a Speed of Life!

ቦርዱ ከፓርቲዎች ለቀረቡለት አቤቱታዎች ምላሽ እንዲሰጥ ለሚመለከታቸው አካላት ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፓርቲዎች ለቀረቡለት አቤቱታዎች ምላሽ እንዲሰጥ ለሚመለከታቸው አካላት ጥሪ አቀረበ።

ቦርድ በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ሰሞኑን ከተለያዩ ፓርቲዎች የቀረበለትን አቤቱታ አስመልክቶ ምላሾችን መስጠቱን አስታውቋል።

በዚህም መሰረት፥ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ትዴፓ/ እስር፣ ማስፈራራትና ቢሮ መዘጋት እንዳጋጠመው እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ /ኢዜማ/ ስብሰባዎች መሰናከል፣ በጎንደር በደብረብርሃን እና የጸጥታ ሃይሎች ለመሰናከሉ ትብብር አድርገዋል የሚል ቅሬታ እንደቀረበለትም ገልጿል።

በተጨማሪም ኦሮሚያ ብሔራዊ ፓርቲ /ኦብፓ/ እስራት፣ ቢሮ መዘጋት፣ ታፔላ መነቀልና አባላት ማስፈራራት እንደደረሰበት፣ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ /ኦፌኮ/- የአባላት እስርና ማስፈራራት፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር /ኦነግ/ የመስራቾች ፊርማ መነጠቅ እና በተለያዩ የኦሮሚያ ክፍሎች የአባላት እስር እየደረሰበት መሆኑን አቤቱታ አቅርበዋል።

የጌዲዮ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት /ጌህዴድ/ ሰነድ መነጠቅና የማሟያ ፊርማ ማሰባሰብ ሂደት መደናቀፍ እየደረሰበት መሆኑን አስታውቋል ብሏል ቦርዱ ባወጣው መረጃ።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድም ፓርቲዎቹ ያቀረቡትን አቤቱታ በማያያዝ የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላት ጉዳዩን ከሚያስረዱ ሰነዶች ጋር የካቲት 26 እና 27 ቀን 2012 ዓ.ም በቦርዱ ፅህፈት ቀርበው እንዲያስረዱ ደብዳቤ መላኩንም ነው ያስታወቀው።

በዚህ መሰረት ለአቤቱታዎቹ ምላሽ እንዲሰጡ ለትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መስተዳድር፣ ኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መስተዳድር፣ ለአማራ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ፖሊስ ኮሚሽን፣ ለኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን እና ለኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ባቱ ፖሊስ መምሪያ ጥሪ ማቅረቡን ከቦርዱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.